Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከጉራጌ ዞን ተወካዮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከጉራጌ ዞን ተወካዮች ጋር በአገና ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው እንደገለጹት፥ የህብረተሰቡን መሰረታዊ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ከምንም በላይ የአካባቢን ሰላም ማስፈን ይቀድማል።

ህብረተሰቡ እያነሳ ያለው ጥያቄ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሁሉንም ነገር በሰከነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የማህበረሰቡን የቆየ ባህል እና እሴት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የትኛውም አይነት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ህዝቡን ዋጋ በማያስከፍል ሁኔታ መቅረብ አለበት ሲሉም ጠቁመዋል።

መደማመጥና መግባባት ከቻልን ችግሮችን በቀላሉ መፍታት ይቻላል ያሉት አቶ እርስቱ፥ በህብረተሰቡ መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለመፍታት የዞኑ ህብረተሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

አመራሩ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች በመደማመጥ እና በመግባባት ላይ ተመስርተው ለአካባቢ ልማት እና ለውጥ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ እርስቱ፥ በህዝቦች መካከል መቃቃርን በመፍጠር የግል አጀንዳቸውን ከሚያራምዱ አካላት ህብረተሰቡ እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት የዞኑ ህዝብ በመንገድ በውሀ በመብራት እና በሌሎችም የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ላይ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የዞኑ መንግስት ትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.