ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በሁለንተናዊ ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ የሞሮኮ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግስት የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ አምባሳደር ንዝሃ አላውዊ ሚሃምዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ትብብራቸውን በሁለንተናዊ ዘርፎች ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
አፈ-ጉባዔው ሁለቱ ሀገራት የቆዬ የወዳጅነት ታሪክ እንዳላቸው አውስተው፣ ይህ ወዳጅነት በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እየተጠናከረና በአፍሪካዊ የወንድማማችነት ስሜት እየጎለበተ መሄድ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
የሃገራቱ ትብብር በዋነኝነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆን እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡
ከዚህም አንጻር ሁለቱን ሕዝቦች የሚመለከቱ ሥራዎች በፓርላማው በኩል እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ንዝሃ በበኩላቸው፤ ሞሮኮ እና ኢትዮጵያ ከነገሥታቱ ዘመናት የጀመረ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላቸው አስታውሰው፤ ይህን ወዳጅነት ለማጠናከርም ሁነኛ የልማት ትብብር መመስረቱን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በአህጉሩ የምትጫወተውን ሚና ሞሮኮ በአድናቆት እንደምትመለከት የጠቀሱት አምባሳደሯ ምንም እንኳን ሁለቱ ሀገራት ራቅ ያለ አሰፋፈር ቢኖራቸውም የሚያመሳስላቿው እና የሚያስተሳስራቿው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አምባሳደሯ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ሞሮኮን እንዲጎበኙ ጋብዘው፤ ሕግ አውጭው አካል ከመሰል የሕግ አውጭ አካል ጋር በጥልቀት ተወያይቶ የተጀመረውን ግንኙነት እንዲያጎለብት መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡