ጥበብ ለሀገር ክብር የተሰኘ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ስራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ግብረ ሀይል ጥበብ ለሀገር ክብር የተሰኘ ግብረ ሀይል አቋቁሞ ስራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ግብረ ሀይሉ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳታወቀው ከቀናት በፊት የህወሓት አጥፊው ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዟል።
የመከላከያ ሰራዊት የሀገር እና ህዝብን ሰላም በመጠበቅ የተለያዩ ግዳጆችን በብቃት ከመወጣት አልፎ ለተለያዩ የሙያ ዘርፎች የራሱ አበርክቶ ያለውና የኪነ ጥበብ ሙያው ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ድርሻው የላቀ ነው ብሏል፡፡
ለዚህ የሀገር ደጀን መከላከያ ሰራዊትም ህዝቡ ያለውን ክብር እና ድጋፍ እንዲገልፅ ጠይቋል፡፡
በግብረ ሀይሉ አስተባባሪነት ማክሰኞ ህዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ከ5 ሰአት ጀምሮ ለሰላሳ ደቂቃ ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ በሚል መሪ ቃል ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በያለበት ቆሞ ለሰራዊቱ ያለውን ክብር የሚገልፅበት ቀን መሆኑን አስታውቋል።
ግብረ ሀይሉ በቀጣይም ለሀገር ክብር ሰው አልባ የሙዚቃ ድግስ፣ ለሀገር ክብር አስራት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እና ለሀገር ክብር ማዕድ የተሰኙ ዝግጅቶችን እንደሚያካሂድም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
በትዝታ ደሳለኝ