ህብረ ብሄራዊነት የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ መሆን እንዳለበት የሀረሪ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዘመናት ቅብብሎሽ ያካበቱት ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴቶችና የማንነት መገለጫዎች አንዱን ከሌላው የሚለዩ መስፈርቶችና ድንበሮች ሳይሆኑ የህብረ ብሄራዊነት፣ የጥንካሬና የአንድነት ምንጮች አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ የህብረ ብሄራዊነትና የአንድነት ችቦ ዛሬ ከሶማሌ ክልል ሀረር ከተማ ሲገባ በተዘጋጀው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ህብረ ብሄራዊነት አንድነትን የሚያጠብቅና ብልጽግናን የሚያፋጥን የጋራ እሴት አድርጎ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
በቃል እንጅ በተግባር ሰፊ ክፍተት የነበረውን የሃገሪቱ የብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የእኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተሟላ ደረጃ ለመመለስ የሚደነቅና የሚበረታታ ርቀት መጓዝ መቻሉን ጠቅሰው ያም ሆኖ እኩልነትን ከወንድማማችነት ጋር አስተሳሰሮ አንድነትና ብልጽግናን ከማረጋገጥ አንጻር አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በመነሳት “እኩልነትና ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል እንደሌሎች በዓላት በደስታና በፌሽታ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ሳይሆን እጅ ለእጅ በመያያዝ መሪ ቃሉ የሚተገበርበትና ወደ ሚታይ ውጤት የሚቀየርበት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የህብረ ብሄራዊ አንድነት ችቦው አቀባበል የደም ልገሳና የበጎ ፍቃድ ማህበራዊ አገልግሎትን እንደሚያካትት ጠቁመው መላው የክልሉ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ህይወትን የሚታደግ ታላቅ የደም ስጦታ እንዲያበረክቱና በበጎ ፍቃደኝነት ማህበራዊ አገልግሎት ተግባራት በስፋት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የህወሓት የጥፋት ቡድንን ለመመንጠርና ለህግ ለማቅረብ በከፍተኛ ጽናት፣ ቆራጥነት፣ ብቃትና ጀግንነት ተልዕኮውን በመወጣት ላይ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት የሀረሪ ክልል ህዝብና መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ከሐረሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡