በድሬዳዋ ከተማ የጥፋት ተልዕኮ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ የጥፋት ተልዕኮ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
ድሬዳዋን ከጎረቤት ሀገራት የሚያገናኙትን በሮች ከሽብርተኞች ለመከላከል ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝም ተመልክቷል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ በህዝብ ጥቆማ መሰረት ሰሞኑን በተለያዩ ቀናት በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።
በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ዘጠኝ ሽጉጦች እንዲሁም ጥይቶች፤ የተለያዩ ሀገራት ፓስፖርቶችና ሰነዶች እንደተገኘባቸው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የጥፋት ቡድኑን ለመደገፍ በለገሀሬ እና ጀርባ በሚባሉ ሰፈሮች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኮሚሽነር አለሙ ገለጻ ÷ድሬዳዋን ከህወሃት ጁንታና ሌሎች ሽብርተኛ ቡድን ተላላኪዎች ለመጠበቅ ምክር ቤት ተዋቅሮ ከኢሚግሬሽን፣ ኤርፖርት፣ ጉምሩክ፣ ፌዴራልና ከተማ ዋና ዋና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር የጠበቀ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል።
ከፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ከሚሊሻ ጋር ተመሣሣይ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነሩ÷ በተለይ ማህበረሰብ ዓቀፍ የፖሊስ ተቋማትና ወጣቶች ለአካባቢው ፀጥታ መጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ድሬዳዋን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኛት መሠረተ ልማቶች፣ የወጪና ገቢ ንግድ መስመሮችን ያገናዘበ የመከላከል ሥራ ከምስራቅ ተጎራባች የፀጥታ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ከሲቲ ዞን፣ ሐረሪ ክልልና፣ ከምስራቅና ከምዕራብ ሐረርጌ ኦሮሚያ ዞኖች ጋር የጋራ እቅድ በማውጣትና ተግባራቱን በመገምገም ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።