Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚሆን ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በድጋፍ ተሰብስቧል- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በድጋፍ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች እና አርሶ አደሮች በዛሬው እለት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ143 በላይ በሬዎች በግ እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ከ95 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርገዋል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችና አርሶ አደሮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች እና መላው ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰጡት ሞራል እና ድጋፍ እጅግ የሚያኮራ ነው ብለዋል።
በተከማዋ ባለፉት ጥቂት ቀናት ለሰራዊቱ በተደረገው ድጋፍም ከ1 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡንም ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
በቀጣይ ቀናትም ለሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ወይዘሮ አዳነች፥ ድጋፉን ያስተባበሩ እና ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።
የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች እና አርሶ አደሮች 90 ነጠብ 8 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም 143 ሰንጋ በሬዎች፣ 115 በግ እና ፍየል እንዲሁም ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በጠቅላላው ከ95 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ለሀገር መከላከያ ድጋፍ መደረጉን የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን አምባዬ ገልጸዋል።
ክፍለ ከተሞቹ ያደረጉትን የገንዘብ፣ የሰንጋ በሬ እና ሌሎች ድጋፎችን ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚንስትር ደኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉጂ እና ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ማስረከባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክረተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.