የአዲስ አበባ የህክምና ባለሙያዎች በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ለማገዝ ወደ ስፍራው አቀኑ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የጤና ተቋማት የተውጣጡ 48 የጤና ባለሙያዎች መንግስት በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለማገዝ ወደ ስፍራው አቀኑ።
በሁለት አቅጣጫዎች ወደ ስፍራው ለሚያቀናው የጤና ባለሙያዎቹ ቡድንም በዛሬው እለት ሽኝት ተደርጓል።
በሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ እና ጀነራል ጥጋቡ ይልማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ እንደመከላከያ ሰራዊቱ ሁሉ የህክምና ባለሙያዎች የተለያዩ ችግሮች ሲያገጥሙ የህብረተሰቡን ህይወት በማዳን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፣ በማድረግም ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከደሞዛቸው በተጨማሪ በሙያቸው ሰራዊቱን ለማገልገል ለመሄድ በመወሰናቸው ምን ያክል ሀገር ወዳድነታቸውን የሚያሳይ ተግባር በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምክትል ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩም የህክምና ባለሙያዎቹ የሚስፈልጋቸውን ሁሉ ለሟሟላት ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ የጤና ባለሙያዎች በሄዱበት ተልዕኮ በድል እንዲመለሱ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን ለማገዝ ወደ ስፍራው ያቀኑት የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው የሀገር ጥሪን በመቀበል ሰራዊቱን በሙያቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሙያቸው ለማገልገል ከሚጓዙት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላን ጨምሮ 10 ስፔሻሊስት ሀኪሞች፣ 24 ነርሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 48 የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለጤና ባለሙያዎቹ ወጪን ጨምሮ የህክምና ቁሳቁሶች እና ሁሉንም አስፈላጊ ግብአቶች አሟልቷል።
በለይኩን ዓለም