Fana: At a Speed of Life!

አቶ እርስቱ ይርዳው ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ደም ለግሰዋል፡፡

አቶ እርስቱ ይርዳው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከሀዲው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ አመራሩ ደም ለመለገስ ቃል በገባው መሠረት ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡

ሀገርን ለማዳን በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ደም ከመለገስ ባለፈ በገንዘብ በአይነትና እና በሌሎችም ድጋፍ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ክልሉ የክልሉ ህዝብና መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ እርስቱ ገለጻ ዘራፊውና ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም በክልሉ አለመረጋጋት እንዲኖር ሀብት መድቦ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ሲያሴር ነበር፡፡

ወንበዴው ቡድን ለህግ እስከሚቀርብ ድረስ ለመከላከያ ሀይሉ የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚቀጥል ጠቅሰው÷ የመከላከያ ሀይሉ የትግራይን ህዝብ ነጻ ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት የክልሉ መንግስት ይደግፋልም ነው ያሉት፡፡

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው÷ የክልሉ ህዝብ ሀገርን ለማዳን ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ያለውን በሙሉ እንሰጣለን በሚል ህዝቡ ዳር እስከ ዳር የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር አመራሩ የድርሻውን እየተወጣ ነው ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.