የሀገር ውስጥ ዜና

የጋምቤላ ክልል አመራሮችና ነዋሪዎች በህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ደም ለገሱ

By Tibebu Kebede

November 16, 2020

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጋምቤላ ክልል አመራሮችና ነዋሪዎች በህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ደም ልገሳ መርሃ ግብር በጋምቤላ ከተማ አካሂደዋል።

ከአመራሮቹ መካከል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላክዴር ላክባክ እንዳሉት፥ ጽንፈኛውና ዘራፊው የህወሓት ቡድን በሀገር አለኝታ በሆነው በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ደም እየለገሱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ሀገርን ለማዳን በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ደም ከመለገስ ባለፈ በገንዘብና በሌሎች ድጋፍ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች አስፈላጊውን ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ጽንፈኛው ቡድን ለህግ እስኪቀርብ ድረስ ለመከላከያ ሰራዊት የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ላክዴር ተናግረዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው፥ ሀገርን ለማዳን ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን በሙሉ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህገ-ወጡን ህወሓት ወደ ህግ ለማቅረብ ተኪ የሌለው ህይወታቸውን መስዋዕት እያደረጉ ለሚገኙ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሊተካ የሚችል ደም መለገሳቸው ኢምንት መሆኑን አስታውቀው በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

በዛሬው ዕለት የተጀመረው ደም የመለገስ መርሃ ግብር በቀጣይ ቀናትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሰክረተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።