Fana: At a Speed of Life!

የአንበጣ መንጋ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል አቅዶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ እና ከውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጣው ቡድን በክልሎች ተንቀሳቅሶ የአንባጣ መንጋ ያስከተለውን ጉዳት በመስክ ምልከታ ካረጋገጠ በኋላ ባቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ከሚመለከታቸው ተጠሪ ተቋማት ጋር ተወያይቷል፡፡
 
በውይይቱም በአንበጣ መንጋና በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን እንዲሁም ከፀጥታ ስጋት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
 
ግብርና ሚንስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች በውይይቱ የተገኙ ሲሆን የተከሰተውን የአንበጣ መንጋና የጎርፍ አደጋ ለመካለካለ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በቅንጅት በመስራት የዜጎችን ህይወት መታደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
 
የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ እንዳሉት ከሰላም ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን እስከታች ወርዶ በመስራትና በመደገፍ ባህላዊ እሴቶችን በማዳበር፤ የአገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን በማሳተፍ አስቀድሞ የመከለካል ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
 
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው በየክልሎች የሚነሱ ግጭቶች መንስኤዎችን በመለየት ፈጥኖ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ፤ እንዲሁም ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጥኖ በመድረስ ለህበረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
 
የቡድኑ አባላት እንደገለፁት የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ችግሩን ከመነሻው ለመቅረፍ ከጎረቤት አገሮች ጋር በቅንጅት በመስራት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
 
የግብርና ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው የቀረበው ምክረ ሃሳብ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያግዝና ለቀጣይ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
የአንበጣን መንጋ ለመከለካል ያሉት አውሮፕላኖች ጥቅም ሊሰጡ ባለመቻላቸው ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ከሃገር ውስጥና ከውጭ የመጡ አውሮፕላኖችን በጋራ በመጠቀም ችግሩን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም የችግሩ መጠን እና የአቅርቦቱ ሁኔታ ሊመጣጠን ባለመቻሉ አንበጣው በሃገራችን በተለያዩ ክልሎች ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡
 
አክለውም በክልሎች የነበረው የፀጥታ ስጋት በስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በማሳደሩ የህብረተሰቡን ችግር ፈጥኖ ለመቅረፍ ፈታኝ እንደነበር ጠቁመው በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመከላከል ስራውን እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
 
የተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በቀጣይ ክትትልና ደጋፍ በማድረግ በጋር እየገመገሙ መስራት፤ ውጤት ለማምጣት በጊዜ፣ በመጠንና በጥራት ማከናወን ስለሚያስፈልግ መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች መሬት ወርደው ሲፈፀሙ ማየት እና ሁሉም ተቋማት በአጭር እና በረጅም ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራትን ለይተው በእቅድ በመስራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል በማለት ማሳሰባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.