ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር መቆም ለራስ ክብር መቆም ነው – የጋምቤላ ክልል ር/መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር መቆም ለራስ ክብር እንደመቆም ሊቆጠር እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።
“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” በሚል መሪ ቃል የሁለት ደቂቃ መርሃ ግብር በጋምቤላ ክልል ተካሄዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ወቅት፥ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት መላው የጋምቤላ ህዝብን ያስቆጣ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱን እንደሚያወግዙ በተለያዩ መድረኮች ሲገልፁ መቆየታቸውን ጠቅሰው በትናንትናው ዕለትም ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደም መለገስ መርሃ ግብር መጀመሩን አስታውሰዋል።
የህወሓት ጁንታ ለህግ እስከሚቀርብ ድረስ ለመከላከያ ሀይሉ የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።