Fana: At a Speed of Life!

“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” መርሀ ግብር በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” መርሀ ግብር በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተካሄደ፡፡
መርሃ ግብሩ በአፍሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ነው የተካሄደው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችና የማህበረሰቡ አባላት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘም በሱዳን መርሃ ግብሩ የተካሄደ ሲሆን የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮን ጨምሮ የሚሲዮኑ ዲፕሎማቶች፣ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች እና የመከላከያ አታሼ ባልደረቦች ተሳትፈዋል፡፡
እንዲሁም በኬንያ ናይሮቢ፣ ኡጋንዳ ካምፓላ እና በግብጽ ካይሮ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም ዲፕሎማቶችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና አጋርነት አሳይተዋል፡፡
በተመሳሳይ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ እና በኳታር ዶሃ በሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች “ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” መርሀ ግብርን አከናውነዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በሪያድ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አሕመድ፣ ዲፕሎማቶችና መላው የኤምባሲው ማሕበረሰብ ተሳትፈዋል።
ሁሉም ተሳታፊዎች ለአንድ ደቂቃ ቀኝ እጃቸውን በግራ ደረታቸው ላይ አድርገው በመቆም ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር የገለፁ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ ህግን በማስከበር በህዝብና መንግስት የተጣለባቸውን ግዳጅ ሲወጡ በጁንታው ሀይል ክህደት የተሰው የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ተዘክረዋል።
በተጨማሪም በእንግሊዝ ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርሃ ግብሩ የተካሄደ ሲሆን፥ ዲፕሎማቶችና የማህበረሰቡ አባላትም ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፡፡
በቤልጂየም ብራሰልስም መርሃ ግብሩ ሲካሄድ ዲፕሎማቶች እና የኤምበሲው ማህበረሰብ አባላት ለሰራዊቱ ያላቸውን ክብርና አጋርነት አሳይተዋል፡፡
እንዲሁም በስዊድን እና በጀርመን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች መርሃ ግብሩ ተከናውኗል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይም ዲፕሎማቶችና የማህበረሰብ አባላት ለሰራዊቱ ክብርና ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡
“ለሃገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” መርሃ ግብሩ በተመሳሳይ መልኩ በጣሊያን እና ፈረንሳይ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም ተካሄዷል፡፡
መርሃ ግብሩ በእስራኤል እና በሩሲያ ሞስኮ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችም ለሰራዊቱ ያላቸውን ክብርና አጋርነት በማሳየት ተከብሮ ውሏል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.