በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገባ አደንዛዥ እጽ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ ሃገር በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገባ የአደንዛዥ እጽ መያዙ ተገለጸ።
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በተለምዶ ቄሶች ሰፈር በሚባለው አካባቢ በህብረተሰቡ ጥቆማ ከውጭ ሃገር በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገባ አደንዛዥ ዕጽ መያዙን የክፍለ ከተማው ንግድ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
አደንዛዥ እፁ አዲስ እየተሰራ በሚገኝ ህንጻ ምድር ቤት መገኘቱንም የኮልፌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ዋና ሃላፊ ኢንስፔክተር ሃብታሙ አንተነህ ገልጸዋል።
አደንዛዥ እጹ ወደ ህብረተሰቡ ሳይሰራጭ መያዙ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ማስቀረት ተችሏልም ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ህገወጥ ተግባራት ሲመለከት በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት መዋቅርና የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የዘወትር ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።