Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከክፍያ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከክፍያ ጋር በተያያዘ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየፈታ መሆኑን አስታወቀ።

ተገንብተው ወደ ስራ ከገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በቀር የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ፈተና እንደሆነባቸው ይነገራል።

ባለሃብቶችም በተደጋጋሚ የሚያነሱት ቀዳሚው ችግር የሃይል አቅርቦት ሆኗል።

ሃይልን ጨምሮ በፓርኩ ውስጥ ያለውን መሰረተ ልማት ማሟላት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ግዴታ ነው።

ኮርፖሬሽኑ መፈጸም የሚገባውን ክፍያ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመፈጸሙ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃይል አቅርቦት ችግር አለ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ለሊሴ ነሚ የሃይል እጥረት ዋነኛው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ችግር መሆኑን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች መፍትሄ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክ ሃይል በክፍያ የሚቀርቡ አማራጮች ዘላቂ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ መንግስት ቋሚ የሀይል አማራጭ ለመፍጠር እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከቻይና መንግስት ጋር ስምምነት መፈራረሙንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የራሳቸው የሃይል አማራጭ እንዲኖራቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለሙከራ የሚሆኑ ፓርኮች ተመርጠው ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በዚህም የጸሃይ፣ የንፋስ እና የእንፋሎት አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ጥናቶች እየተካሄዱ ሲሆን፥ በጸሃይ ሃይል አማራጭ ላይ የግሉ ዘርፍ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ተስተውሏልም ነው ያሉት።

በጥናቱ ውጤት መሰረት ስራውን ወደ ተግባር መቀየር ይቻል ዘንድ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና የአዋጭነት ጥናቶች ከወዲሁ እየተሰራባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

እየተካሄደ ያለው ጥናትም በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በትእግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.