Fana: At a Speed of Life!

ማህበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ማህበረሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መከላከል እንደሚገባው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነውን ሠላም ለመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ኮሚሽኑ አስገንዝቧል፡፡

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የስልጠና እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዐቢይ ሙሉጌታ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ያሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር እና አዳዲስ መረጃዎችን በማድረስ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ማህበረሰቡ ባደረገው ጥቆማም በወልድያና ባሕር ዳር ከተማ ለሽብር የተዘጋጁ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ቤተ እምነቶች በፌደራል ፖሊስ፣ በድርጅቶችና በራሱ በማኅበረሰቡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ትብብር አጠናክሮ በማስቀጠል አካባቢውን ከሕወሓት ቅጥረኛ ቡድን ሊጠብቅ እንደሚገባ መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችም ህወሓት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መሰሎቹን አሰማርቶ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመከላከል ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.