Fana: At a Speed of Life!

እምቦጭን ከጣና ሀይቅ ለማስወገድ ሲካሄደው የነበረው ዘመቻ እስከ ሕዳር 30 እንዲቀጥል ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከጣና ሐይቅ ላይ እምቦጭን ለማስወገድ ለአንድ ወር ሲካሄድ የነበረው ዘመቻ እስከ ሕዳር 30 እንዲቀጥል ተወሰነ።
እስካሁን በነበረው ዘመቻ ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበ የዘመቻው አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የዘመቻውን መራዘም አስመልክቶ የዘመቻው አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ ዛሬ ማምሻውን በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ከጥቅምት 9 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ሲካሄድ በቆየው ዘመቻ በተለያዩ ምክንያቶች ሁሉንም ቀናት መጠቀም ባለመቻሉ የዘመቻውን ጊዜ እስከ ኅዳር 30 ማራዘም አስፈላጊ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
እስካሁን በነበረው የዘመቻ ጊዜ አረሙን በማስወገድ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መታየቱም ተገልጿል፡፡
በመግለጫውም በእስካሁኑ ዘመቻ የእምቦጭ አረም ተከስቶባቸው ከነበሩት 30 ቀበሌዎችን ከሚያዋስነው የሐይቁ አካል በ17 ቀበሌዎች ውስጥ የተከሰተውን አረም ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
በዘመቻውም ከ200 ሺህ በላይ የሰው ኃይል መሳተፉ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
የአብይ ኮሚቴው አባልና በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመስኖና ድሬኔጅ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ እስካሁን ለዘመቻ ው 125 ሚሊየን
ብር መገኘቱን ገልፀዋል።
በዘላቂነት አረሙን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ 300 ሚሊየን ብር ያህል የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዘመቻ ሥራው አረሙን የመንቀል ብቻ ሳይሆን አድርቆ የማቃጠል ካልሆነም የመቅበር እንዲሁም በዘላቂነት አረሙን ለመቆጣጠር በሃይቁ ዙሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአብይ ኮሚቴው አባልና የአማራ ክልል ውሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው በበኩላቻ የእምቦጭ አረም የተንሰራፋባቸው 30 ከሃይቁ አዋሳኝ ቀበሌያት ውስጥ ከ17ቱ ሙሉ በሙሉ አረሙ መወገዱን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በነበረው የዘመቻ ስራ 60 በመቶ ያህል እቅዱን ማሳካት የተቻለ ሲሆን በተጨማሪው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ቀሪውን እቅድ የማሳካት ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድም እምቦጭን ከ17ቱ የሐይቁ አዋሳኝ ቀበሌያት ማስወገድ መቻሉ ከፍተኛ ውጤት መሆኑን ጠቁመው ከተቀሩት ቀበሌዎች ጨርሶ ለማስወገድ በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 30 ቀናት በተካሄደው ዘመቻ የአካባቢው ነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን የገለጹት ዶክተር አዳነች በቀጣይም አረሙ በተከሰተባቸው ከሌሎች የውሃ አካላት ላይ በተባበረ ክንድ ማስወገድ እንደሚቻል ተሞከሮ የሚወሰድበት ዘመቻ እንደሆነም መናገራቸውን ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዘመቻም ሁሉም ዜጋ በትብብር ከሠራ የማይቻል ነገር እንደሌለ ያረጋገጥንበት ነው ያሉ ሲሆን በዘመቻው ከፍተኛ ተሳትፎ ላደረጉት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.