ከፅንፈኛው ህወሃት እና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብው የተጠረጠሩ 287 ሰዎች ከጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል- ፌዴራል ፓሊስ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ባለፉት 14 ቀናት በተካሄደ ዘመቻ ከፅንፈኛው ህወሃት እና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 287 ሰዎች ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መወላቸውን የፌዴራል ፓሊስ አስታወቀ።
ፅንፈኛው የህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ሲጠብቁ በነበሩ የፌዴራል ፓሊስ አባላት ላይ በፈፀመው ጥቃት ግድያ እና አፈና መፈፀሙን ኮሚሽኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ አስታውሷል።
ይህ ቡድን በመሀል ሀገርም ሊያደርስ የሚችለውን ማንኛውንም ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ከእኩይ ተግባራቸው ለመግታት የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላለፉት 14 ቀናት ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በዚህም አንድንድ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ለሀገር እና ለህዝብ ስጋት የሆነ ተግባር ላይ መሰማራታቸው እንደተደረሰበት ነው ኮሚሽኑ የገለፀው።
ለአብነት ሱር ኮንስትራክሽን በተባለው ድርጅት ላይ በተደረገ ህጋዊ ብርበራና ፍተሻ ለተለያዩ ዘመቻዎች የተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ፣የፀሀይ ሀይል ማመንጫ ፣ ተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ወታደራዊ ሬዲዮ መገናኛዎች በህንፃው ምድር ቤት ተሸሽጎ እንዳለ መያዙን የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን በመግለጫ ላይ አስታውቋል።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከፅንፈኛው ህወሃት እና ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 287 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርምራ እየተካሄደባቸው ነው ተብሏል።
በከተማዋ በተደረገ ብርበራ ፣ ፍተሻ ፣ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ፣ በፖሊስ አሰሳ እና ከግለሰቦቹ እና ከተጠረጠሩ ተቋማት 1 ሺህ 32 የተለያዩ ጠመንጃዎች ፣ 131 የተለያዩ ሽጉጦች እና 46 ሺህ 39 ጥይቶች ተይዘዋል።
እንዲሁም 14 ቦምቦች፣ 1 ፈንጂ፣ 5 ጂ ፒ ኤስ ፣8 የጦር ሜዳ መነፀር ፣5 ካቴና ፣55 የክላሽ መጋዘን እና እጀታ ፣ 1 ሺህ 339 የተለያዩ የኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች ፣845 ሺህ 434 የሀገር ውስጥ ገንዘብ እና 227 ሺህ 271 የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች እንደተያዙ ነው ፓሊስ የገለፀው።
በተጨማሪም የተለያዩ የሰራዊት አልባሳት ፣ ፓስፖርቶች ፣ የውጭ ሀገር የስራ ፍቃድ ሰነዶች፣ በርካታ ገንዘብ ያዙ የባንክ ደብተሮች ፣ በሽጉጥ ላይ የሚገጠም የድምፅ ማፈኛ ፣ የተለያዩ ኮምፒዩተሮች፣ ፀረ ታንክ መሳሪ እና ሌሎች መሳሪያዎች መያዛቸውም ተጠቁሟል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ከሚገኘው ዘመቻ ጋር ተያይዞ የጥፋት ሀይሉ ተላላኪዎች ሊጠቀሙባቸው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ሆን ብለው ዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ በሚችል መልኩ በየቦታው ጥለዋቸው የነበረ ቢሆንም ፓሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ሊያከሽፋቸው እንደቻለ ነው የተገለፀው።