Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ በፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አገጣጠም ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ

አዲስ አበባ ፣ህዳር 10 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አገጣጠም ሁኔታ ላይ ከሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት ማህበራት እና ከፍጥነት መገደቢያ ገጣሚ ድርጅቶች ጋር ውይይት አደረገ፡፡
በፍጥነት ምክንያት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በየደረጃው ሁሉም ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ እንዲገጥሙ በተወሰነው መሰረት የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች መሳሪያውን እንዲገጥሙ እየተደረገ ይገኛል ተብሏል፡፡
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀውም በዚህ ሂደት ላይ ያለውን አፈጻጸም ለመገምገም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ÷ በመሳሪያው አገጣጠም ሂደት ላይ የተወሰኑ ክፍተቶች መስተዋላቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ክፍተቶችን ለማስተካከል የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ የሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻ ድርጅቶች እና የፍጥነት መገደቢያ ገጣሚ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ በመነጋገር መፍትሄ ለማስቀመጥ እና ስራው በተሳካ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ ውይይቱ ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡
በእለቱም በህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መገጠም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት የቀረበ ሲሆን ÷ በሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻ ማህበራት፣ በፍጥነት መገደቢያ ድርጅቶች እና በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችም ቀርበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የሁሉንም አካላት ድርሻና ሀላፊነት ያካተተ እና ያጋጠሙ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉበትን መንገድ ያመላከተ የመፍትሄ ሀሳብና የድርጊት መርሀ ግብር መቅረቡን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.