Fana: At a Speed of Life!

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጎንደር፣ በአሰላ ፣ በሚዛን አማን እና በወላይታ ሶዶ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጎንደር፣ በአሰላ ፣ በሚዛን አማን እና በወላይታ ሶዶ የፋና ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ተከብሯል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98 ነጥብ 1 የሬዲዮ ጣቢያ 12ኛ ዓመት የምስረታ በአል በጎንደር ከተማ ተከብሯል።
በምስረታ በዓሉ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የለውጥ ጉዞን የሚያስቃኝ ፅሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ፥ ፋና በሬዲዮ ስርጭቱ በአካባቢው ተደራሽ በመሆኑ በወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎች ህዝብና መንግስትን እያገናኘ ውጤታማ ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
“የጎንደር ፋና ኤፍ ኤም በአካባቢው ብቸኛ በመሆኑ የሚያበረክተውን ማህበራዊ ፋይዳ በመረዳት ከጎኑ በመሆን ስንሰራ ቆይተናል” ያሉት አቶ ሞላ፥ “በቀጣይም ለተሻለ ስራ ሚዲያውን በማገዝ በለውጥ ጉዞው አብረን እንጓዛለን” ነው ያሉት።
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሳተፉት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ፥ ፋና ላለፉት 25 ዓመታት ችግሮችን በመንቀስና ልዩ ልዩ ይዘቶችን በመዳሰስ ወደ አድማጮች ሲደርስ በመቆየቱ የሚያስመሰግነው መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም ለላቀ ውጤት በሙያ ድጋፍና በሌሎች ዘርፎች ከተቋሙ ጋር እንሰራለን ብለዋል።
በተመሳሳይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና የአሰላ ፋና ኤፍ ኤም የምስረታ በዓል በአዳማ ከተማ ተከብሯል።
በአዳማ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይም የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አድማጭ ተመልካቾች፣ ሰራተኞችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የ25 ዓመታት ጉዞ እና የዲጂታል ሚዲያ ጅማሮዎች በሚል የውይይት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም ፋና ቀዳሚ ምርጫቸው መሆኑን ያነሱ ሲሆን፥ ከስርጭት ተደራሽነት አንፃር መስራት አለበት የሚሉ ሀሳቦች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የፋና 25ኛ ዓመት ክብረ በዓልና ሚዛን አማን ፋና ኤፍ ኤም 92 ነጥብ 5 ምሥረታ በዓል በሚዛን አማን ከተማ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ የሚዛን አማን ፋና ኤፍ ኤም ደንበኞች ፣ ተባባሪ አካላት እና የጣቢያው ሠራተኞች ታድመዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ አቶ ዘማች በዛብህ ÷ፋና በአካባቢው ልማትና ማሕበራዊ ጉዳዮች እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
ተሳታፊዎችም ጥያቄና አስተያየት የሰጡ ሲሆን ÷ ፋና በአካባቢው ያለውን አዎንታዊ ሚና አድንቀዋል።
የሚዛን አማን ፋና ችግሮች እንዲቀረፉ ፣ የአካባቢው ባህል እንዲተዋወቅና እንዲለማ አስተዋፅኦ አበርክቷልም ነው ያሉት።
ከዚም ባለፈም ተሳታፊዎቹ በጣቢያው ተጨማሪ ቋንቋዎች ስርጭት እንዲኖርም ጠይቀዋል ።
የጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ ተራመድ ጥላሁን ጣቢያው ከሕዝብ የሚሰጡትን ሀሳቦች እንደ ግብአት በመጠቀም በቀጣይ ሕብረተሰቡን ተደራሽ የሚያደርጉ ሥራዎች እንዲሚሰሩ ገልጸዋል።
በተመሳሳይም የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ አመት ምስረታ በዓል በወላይታ ሶዶ ፋና ሬዲዮ ጣቢያ በዛሬው ዕለት ተከብሯል።
በዚህም የፋና 25ኛ ዓመት ምስረታ በዓልና ፋና ከየት ወደየት በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
በውይይቱ የወላይታ ሶዶ ፋና ሬዲዮ ጣቢያም የ 9 አመታት ጉዞም የተቃኘ ሲሆን÷ ጠንካራና ማሻሻያ የሚያስፈልጓቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ከተጋባዥ ዕንግዶች እና አድማጮች አስተያየትም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በቀጣይ ጊዚያት አዳዲስና አሳታፊ ፕሮግራሞች እንደሚካተቱም ተገልጿል።
በመጨረሻም ከጣቢያው ጋር የሰሩና እየሰሩ ለሚገኙ የተለያዩ መንግሥታዊና የግል ተቋማት የዋንጫና የሰርተፊኬት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እስካሁን በጅማ፣ ሻሸመኔ፣ ሐረማያና በደሴ እና በደብረ ብርሃን መከበሩ የሚታወስ ነው።
ምንጭ፡- በሙሉጌታ ደሴ ፣አፈወርቅ እያዩ እና በጥላሁን ሁሴን

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.