በኦሮሚያ ክልል የአራት ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት 530 ሰንጋዎችን እና ከ13 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሃረርጌ፣ የባሌ፣ የጅማ እና የጉጂ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት 530 ሠንጋዎችን እና ከ13 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
ከአራቱም ዞኖች የተወከሉ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግስት ሃላፊዎች የነዋሪዎቹን ድጋፍ ዛሬ በምድር ሃይል ግቢ ተገኝተው አስረክበዋል፡፡
የምስራቅ ሃረርጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የድርጅት ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን እንዳሉት÷ የዞኑ ነዋሪዎች 418 ሰንጋዎችን፣ 100 ኩንታል የፉርኖ ዱቄት፣ 89 ፍየሎችን እና 50 ኩንታል ስኳር አበርክተዋል፡፡
የባሌ ዞን ድጋፍን ያስረከቡት የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰይፈዲን ሃሰን ግምታቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ 38 ሰንጋዎችን ለመከላከያው ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የነገሌ ከተማ ከንቲባ አቶ በቀለ ቢራ የጉጂ ዞን 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር፣ 74 ሰንጋ፣ 61 ፍየሎችና 12 በጎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
የጅማ ዞን ነዋሪዎችም የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያሏቸው ቁሳቁሶችን ለሰራዊቱ ያበረከቱ ሲሆን በተመሳሳይ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 150 ፍየሎችና አንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከዞኖቹ የህዝቡን ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊቱ ለማስረከብ በምድር ሃይል የተገኙት የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማት አባቶች ህዝቡ ከሰራዊቱ ጎን መቆሙን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡