የብር ኖት ቅያሬ ታህሳስ 6 ቀን እንደሚጠናቀቅ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሮጌው ብር ኖት ቅያሬ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ከመስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አሮጌ የብር ኖቶች በአዲስ የብር ኖቶች እየተቀየሩ መሆኑን ያስታወሰው ባንኩ፥ የብር ኖት ቅያሬው በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መወሰኑን አስታውቋል።
እስካሁን ያለው የብር ኖት የመቀየር ሂደት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም ነው ባንኩ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
የብር መቀየሪያው ቀን ሊጠናቀቅ 25 ቀናት ብቻ እንደቀሩት በመጥቀስም በቀሪዎቹ ቀናት ያልተቀየረ ብር እንዲቀየር እና ሂደቱን ለማፋጠን ከህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት 15 ቀናት በአሮጌው ብር ግብይት መፈፀም እንደማይቻልም ባንኩ አስታውቋል።
በእነዚህ 15 ቀናትም ማንኛውም ሰው በእጁ የሚገኝ አሮጌውን ብር ወደ ባንክ ሄዶ መቀየር ግን ይችላል ብሏል ባንኩ።
ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም የመጨረሻው የአሮጌ ብር ኖት መቀየሪያ ቀን መሆኑ ታውቆ ህብረተሰቡ በእጁ ያለውን አሮጌ ብር እንዲቀይርም ብሄራዊ ባንክ አሳስቧል።
የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር እና የፀጥታ አካላትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡ ባንኩ ጥሪ አቅርቧል።