መንግስት በህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ለወዳጅ ሀገራት እያስረዱ መሆኑን በሩስያ እና በቱርክ የሚገኙ የኢትዮዽያ አምባሳደሮች ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ህዳር 10 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት በፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ ህግ ለማስከበር እየወሰደ ስላለው እርምጃ ለወዳጅ ሀገራት እያስረዱ መሆኑን በሩስያ እና በቱርክ የሚገኙ የኢትዮዽያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች ተናገሩ።
በሩስያ የኢትዮዽያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ እና በቱርክ የኢትዮዽያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ግርማ ተመስገን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በስልክ ቆይታ አድርገዋል።
አምባሳደሮቹ መንግስት በፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ለተመደቡባቸው ሀገራት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ለሚገኙ ሀገራት እና ዲፕሎማቶች እርምጃ ትክክለኛ መረጃ እየሰጠን ነው ብለዋል።
አምባሳደሮቹ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርም የተግባር እንቅስቃሴ እያካሄዱ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በሩስያ የኢትዮዽያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ፅንፈኛው የህወሐት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ የፈፀመውን ወንጀል እና የሀገር ክህደት እንዲሁም መንግስት ህግ ለማስከበር እየወሰደ ያለውን ዘመቻ አስመልክቶ ፈጣን የሆነ መረጃ ለሞስኮ ዲፕሎማቶች ማድረሳቸውን ተናግረዋል።
አምባሳደር አለማየሁ የኢትዮዽያ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ህግ የማስከበር ተልዕኮ መሆኑንና የዚህ ዋና ተልዕኮ እና ግብም ፅንፈኛውን ቡድን ከንጹሃን በመለየት ህግ ፊት ማቅረብ እንደሆነ እያስረዳን ነውም ብለዋል።
የኢትዮዽያ እና የሩስያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የቆየ ታሪክ ያለው ነው የሚሉት አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ÷ በሩስያ እና አካባቢዋ የሚገኙ ትልደ ኢትዮዽያዊያን እና የኢትዮዽያ ወዳጆች የጁንታው ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ክህደት በከፍተኛ ደረጃ እያወገዙት ነው ብለዋል።
በቱርክ የኢትዮዽያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ግርማ ተመስገን በበኩላቸው÷ ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ታላቅ ታሪክ ባለው መከላከያ ሰራዊት ላይ የሀገር ክህደት መፈፀሙንና በመንግስት እየተወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃ ለቱርክ ሰዎች በግልፅ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ግርማ አያይዘውም የፅንፈኛውን ቡድን አሳፋሪ ድርጊት እና ከባድ የሀገር ክህደት ወንጀል እያስረዱ ያሉት ለቱርክ ብቻ ሳይሆን በአንካራ ለሚገኙ የምስራቅ አፍሪካ ዲፕሎማቶች ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን ስራ እያከናወኑ ያሉት ደግሞ በተናጥል ሳይሆን በቱርክ ከሚገኙ የኢትዮዽያ የክብር ቆንስላ ፅፈት ቤቶች ጭምር መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
አምባሳደር ግርማ የፅንፈኛውን ቡድን ተግባር ለመንግስታት እና ዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆን እያስገነዘቡ ያሉት ለምሁራን እና ለሀሳብ አፍላቂ ትላልቅ ተቋማት ጭምርመሆኑን ተናግረዋል።
ከዚያም ባለፈ የኢትዮዽያ እና የቱርክን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ከመደበኛው የዲፕሎማሲ ስራ በተጨማሪ በዲጂታል ዲፕሎማሲውም ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሁለቱ አምባሳደሮች አሁን ላይ በኢትዮዽያ እየተካሄደ ያለው ህግን የማስከበር እርምጃ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከየሀገራቱ እንደ ከአሁን ቀደሙ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስት መንት ተሳታፊ ኩባንያዎች ጋር በስፋት እየሰሩ መሆናቸውን ም ተናግረዋል።
በስላባት ማናዬ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።