Fana: At a Speed of Life!

ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያንን መመለስና ማቋቋም ላይ የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 10 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሕግ ማስከበር ሂደቱ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያንን ወደቀዬአቸው መመለስና ማቋቋም ላይ የሚሰራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገባ።
የህወሓት የጥፋት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሱ ተከትሎ መንግስት በክልሉ ሕግን የማስከበር ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።
በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ እንደገለጹት፤ የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ዘመቻውን በሚያካሂድበት ከሁመራ፣ ማይካድራና በረከት ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሱዳን ገብተዋል።
ነዋሪዎቹ ዘመቻው በተጀመረ ማግስት በመደናገጥ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሕግ የማስከበር ሂደቱን ተከትሎ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያንን መመለስና ማቋቋም ላይ የሚሰራ ብሔራዊ ኮሚቴ በኢትዮጵያ መንግስት ተቋቁሙ ወደ ሥራ መግባቱንና ዜጎችም ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
እንደአምባሳደሩ ገለጻ፤ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የሚገመግም ቡድን ወደ ስፍራው የተላከ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታዎችን ተመልክቶ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል።
ቡድኑ በመስክ ምልከታው የሚያሳውቃቸውን ግኝቶች መሰረት በማድረግ ለዜጎች አስፈላጊው ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከልማት አጋሮችና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ነው አምባሳደር ይበልጣል ያስረዱት።
መንግስት ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራውን ከሱዳን መንግስትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) ጋር በመሆን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በህወሓት የጥፋት ቡድን አማካኝነት ጉዳዩን ሰብዓዊ ቀውስ ለማስመሰልና ዜጎች ወደአገራቸው እንዳይመለሱ ለማድረግ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ “መንግስት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ነው” ብለዋል።
የጥፋት ቡድኑ ታጣቂዎች ከተሰደዱ ዜጎች ጋር ተቀላቅለው ወደሱዳን እንዳይገቡ ከሱዳን መንግስት ጋር በመሆን ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሕግ ማስከበር ዘመቻውን አስመልክቶ የሱዳን መንግስትና በአገሪቱ ያሉ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በግልጽ እንዲገነዘቡት ማብራሪያ መሰጠቱንም ነው አምባሳደር ይበልጣል ያብራሩት።
በሱዳን ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስለ ሕግ ማስከበር ዘመቻው ገለጻ፤ መደረጉንና ኢትዮጵያዊያኑም እርምጃውን ከመደገፍ ባለፈ ለመከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዚሁ ዓላማ የሚውል የሀብት ማሰባሰብ ስራ መጀመራቸውን አምባሳደሩ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.