Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት የአምባገነኑ ጭቆና ነጻ ይወጣል – የብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት የአምባገነኑ ጭቆና ነጻ ይወጣል ሲል የብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።

ዘራፊውና ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ዛሬም ድረስ ምሽግ ውስጥ ሆኖ እጅ አልሰጥም አሻፈረኝ እንዳለ ነው ያለው ፓርቲው፥ ተወደደም ተጠላም የፌደራል መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻውን አጠናክሮ በማስቀጠል እምቢተኛውን የህወሓት ቡድን ለህግ ማቅረቡ አይቀሬ ነው ብሏል፡፡

አምባገነኑ የህወሓት ቡድን ዛሬም እንደትናንቱ ከህዝብና ከሀገር ይልቅ የራስን ምቾት በማስቀደም ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ አያሌ ወጣቶችን አስከፊ ለሆነው ጦርነት መጠቀሚያ እያደረጋቸው ይገኛልም ነው ያለው፡፡

ይህ ግራ የተጋባው ከሃዲ ቡድን መሰረታዊ ዓላማው ሀገርን ማፈራረስ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም ሲልም ገልጿል፡፡

ከተቋማቱ ተልዕኮ ውጭ በሆነ መንገድ በማስፈራራት አልያም ሀይል በመጠቀም መቀሌ የሚገኙ ቤተ እምነቶችን እንደ ምሽግ እየተጠቀመባቸው የገለፀ ሲሆን ቤተ እምነቶችን ለመሳሪያ ክምችት እና ለፕሮፖጋንዳ ስራ መጠቀም ጀምሯል፤ ይህ አይነቱ አካሄዱ በዓለም ላይ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም በማለትም አብራርቷል፡፡

የትኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎም ቢሆን ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን የትግራይን ህዝብ ከአምባገነኑና ከዘራፊው የህወሓት ቡድን ነጻ የማውጣት ተጋድሎ ዛሬም እንደትናንቱ በድል ማጠናቀቁ አይቀሬ ነው ፤ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያውያን ሰላም ናፍቋቸዋል፤ የህግ የበላይነት በተግባር ሲረጋገጥ ማየት ይፈልጋሉና ብሏል፡፡

“መብሰሉ ላይቀር ማጋዶ ይጨርሳል” ነውና ነገሩ ያለው ፅሁፉ ጁንታው የህወሓት ቡድን የቀረበለትን በሰላም እጅ የመስጠት ጥሪ አሁንም የተቀበለው አይመስልም ፤ይህ ደግሞ በሁሉም መልኩ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ማስከፈሉ አይቀርም በማለት የቀጠለ ሲሆን ይህ ቡድን በእምቢተኝነቱ ከቀጠለ እና ሰራዊቱ በሚያደርገው ህግን የማስከበር ዘመቻ የህዝብ መገልገያ ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችና በመሳሰሉት ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ፤ ምክንያቱም ጦርነት ነውና በማለት ገልጿል፡፡

ስለዚህ በየቀኑ የሃሞት ጽዋውን እየተጎነጨ ያለውን ፅንፈኛውና አምባገነኑ የህወሓት ቡድን የመጨረሻ ዕድሉን ተጠቅሞ እጁን መስጠት ካልቻለ ከዚህም በላይ በቁሙ መራራ ጽዋ መጎንጨቱ አይቀሬ መሆኑን በማንሳትም በየትኛውም ሁኔታ ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉበት ዕድል ዝግ ነውና፤  የጣት ቀለበት ያህል መፈናፈኛ እንኳን ማግኘት አይችሉም፣ ጁንታው ያለበት አካባቢ በሙሉ በሰራዊቱ መከበቡን አስታውሷል፡፡

በፅሁፉ የትግራይ ህዝብ የህግ የበላይነት እንዲተገበር ሙሉ ፍላጎት እንዳለው በመግለፅ ለዚህም ነው ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በተለያየ መንገድ እያሳዩ ያሉት ብሏል፡፡

ጁንታው የህወሓት ቡድን አካባቢያችሁን ከጠላት ጠብቁ በማለት ያስታጠቃቸውን ከቀላል መሳሪያ ጀምሮ እስከ ቡድን መሳሪያ ድረስ እኛ ጠላት የለንም እየሆነ ያለው ህግን የማስከበር ስራ ነው በሚል የተቀበሉትን መሳሪያ ለሰራዊቱ እያስረከቡ ያሉት፤ ከዚህ በላይ አጋርነት ምን አለ? ሲልም ይጠይቃል፡፡

ስለሆነም ሰላም ፈላጊው የትግራይ ህዝብ ቤተ እምነቶችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የመሸጉ ጸረ ህዝብ ሀይሎች ለዓመታት ቋጥኙን መንጥሮ፣ ተራራውን ንደው የሰራሀውን መንገድና ድልድይ ከእናንተው ጉያ በተደበቁ ጥቂት አምባገነን ሀይሎች ትዕዛዝና በጀሌዎቻቸው አማካኝነት ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛልና ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍና እነዚህን ጁንታዎች አሳልፎ በመስጠት በደማቁ የሚጻፍ ታሪክ እንዲሰራ ለህዝቡ ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.