Fana: At a Speed of Life!

የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንን የሚያወግዝና መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ተካሄደ።
ሰልፉ ከቤንች ሸኮ ዞን ስድስት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ነው።
ነዋሪዎቹ በሰልፉ የህወሓት ህሊና ቢሡ ጽንፈኛ ቡድን የሀገር ሠላም ዋልታና ማገር የሆነውን መከላከያ ሰራዊት ከጀርባው በመውጋት የፈፀመውን አሳፋሪ ተግባር እናወግዛለን፤ በከሀዲው ቡድን ላይ የህግ የበላይነት እስከሚረጋገጥ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንቆማለን፣ ህወሓትና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኝነት ይፈረጁልን ኢትዮጵያ የውክልና ጦርነት አውድማ አትሆንምና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋል።
በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት 6 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም በዓይነት 82 ሠንጋ፣ 524 ኩንታል ጤፍ፣ 49 ኩንታል ቡና 465 ኪሎግ ራም ማር፣ 50 ኩንታል ሩዝ በድምሩ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን ገልፀዋል።
እንዲሁም ሰልፈኞቹ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚሆን ሀብት የማሰባሰብና የደም ልገሳ እያካሄዱ እንደሚገኙ ከቤንች ሸኮ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.