Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት ግጭት በመፍጠር ላይ የተመሰረተ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ላለፉት ዓመታት ዜጎቹን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማሳሳት ሲሰራበት የቆየ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት ግጭት በመፍጠር ላይ የተመሰረተ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ላለፉት 27 እና 28 ዓመታት ዜጎቹን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማሳሳት ሲሰራበት የቆየ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢለኔ ስዩም ገለጹ፡፡

ኃላፊዋ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ህግ የማስከበር እርምጃ ምክንያት ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ላሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመጨረሻና ወሳኝ የሆነ ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራ በገለጹት መሰረት በርካታ የትግራይ ከተሞችና አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህገ-መንግስቱ በሀገሪቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስልጣንን ለፌደራል መንግስቱና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሰጣል ያሉት ኃላፊዋ፤ አሁን መንግስት እየወሰደ ያለው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እርምጃ በዚሁ መሰረት እየተካሄደ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ህግ የማስከበር እርምጃው የህወሓት አጥፊው ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጫና እንዳሳረፈበት፣ በርካታ ከተሞችንና አካባቢዎችን እየለቀቀና እየሸሸ ቡድኑ እያሸነፈ እንደሆነ መግለጹ ላለፉት 27 እና 28 ዓመታት የራሱን ዜጎችና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ለማሳሳት ሲሰራበት የቆየ እንጂ በፍጹም ሀሰት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል የግንኙነት መስመር በመቋረጡ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልቻለም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም መስመሩ እንዲቋረጥ ያደረገው የፌዴራል መንግስት ሳይሆን አጥፊው የህወሓት ቡድን መሆኑን ጠቅሰው፤ ከግንኙነት መስመሮች በተጨማሪም ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን እያወደሙ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ችግር ምክንያት ወደ ሱዳን እየሸሹ ላሉ ዜጎች እየተደረገ ያለውንም ድጋፍ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደረገ ጥሪ ዜጎች ወደ ሱዳን ከመሄድ ይልቅ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ተቆጣጠራቸው አካባቢዎች እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ለእነዚህ ዜጎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሚሰጣቸው ሰብዓዊ ድጋፍም በፌደራል መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፍ እንየተደረገ እንደሆነና ይህም እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቁት።

በፌደራል መንግስትና በህወሓት ቡድን መካከል ያለውን ችግር በውይይት ለመፍታት የተለያዩ ሀገራት መንግስታትና የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ያቀረበውን ጥያቄ ለምን አልተቀበላችሁም በሚል ለቀረበው ጥያቄም፤ እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ከመገባቱ በፊት ለህወሓት በርካታ የሰላም ጥሪ ቢደረግለትም የተለያዩ ቅደመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ሁሉንም አማራጮች ሳይጠቀም መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡

በአንጻሩ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በማጥቃቱ መንግስት በህገ መንግስቱ የተሰጠውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ቅድሚያ ስራው በመሆኑ ህግ ወደ ማስከበሩ ስራ እንዲገባ ተገዷል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያለፈው ዓመት የሰላም ኖቤል ሽልማትን አሁን ካለው ሀገራዊ ጉዳይ ጋር በማነጻጸር ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ የኖቤል ሽልማቱ ከዚህ ጋር ምንም የሚያገናኘው ጉዳይ እንደሌላ አስረድተዋል፡፡

አሁንም እየተሰራ ያለው ህግ የማስከበርና ሰላም የማረጋገጥ ስራ እንደሆነ መናገራቸውንም ኢዜአ ሲቢሲን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.