የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያዘጋጁት ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያዘጋጁት ውይይት ተካሄደ።
ውይይቱን ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት በአልጀሪያ፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ኔዘርላንድስ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ናቸው።
በውይይቱ ላይ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች፣ የባለሙያዎች ቡድኖች፣ የሚዲያ ተቋማት እና የተለያዩ ሀገራት የፓርላማ አባላት የተሳተፉ ሲሆን አምባሳደሮች ገለፃ አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ በህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላት የሆኑት ዶክተር ዮሀንስ ገብረፃድቅ እና አምባሳደር ረታ አለሙ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ውይይቱን መርተውታል።
በዚህም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ እያካሄዱት ስለሚገኘው ውይይት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ ከሶስትዮሽ ውይይት ጋር ተያይዞ የጋራ በሆኑ ነጥቦች ላይ እና በወሳኝ የቴክኒካል እንዲሁም ህጋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ተሳታፊዎቹ ማብራሪያውን ተከትሎ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ እንደተሰጠባቸው ነው ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያስታወቀው።
ይህ ውይይት ለተሳታፊዎቹ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ ስለሚገኘው ውይይት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ነገሮቹን ግልፅ ያደርጋል ተብሏል።
እንዲሁም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሁኔታ ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ለማሳየት የሚያስችል ውይይት እንደነበረም ተጠቁሟል።