የሀገር ውስጥ ዜና

ሻንግቴክስ ጋርመንት 50 ሚሊየን ዶላር በሆነ ወጪ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጀመረ

By Tibebu Kebede

November 20, 2020

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሻንግቴክስ ጋርመንት 50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሆነ ወጪ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጀመረ።

በግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በኩባንያው የሚገነቡት 3 ሼዶች እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ሜትር ስኩዌር ስፋት ሲኖራቸው ግንባታቸውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በሁለተኛው ምዕራፍም 2 የፋብሪካ ሼዶች እንደሚገነቡ ከኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሻንግቴክስ ጋርመንት ቻይና ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች 2ኛው ግዙፍ ኩባንያ መሆኑ ይነገራል።

ኩባንያው በቦሌ ለሚ ከ50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የሚያከናውነውይህ ኢንቨስትመንት በፓርኩ ከሚገኙ ኩባንያዎች ቀዳሚው ያደርገዋል።