Fana: At a Speed of Life!

በክብር የተሰናበቱና የ20ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አባላትና የመከላከያ የእግር ኳስ ቡድን “ደማችን ለጀግናችን” በሚል መሪ ቃል ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከመከላከያ በተለያዩ ምክንያቶች በክብር የተሰናበቱና የ20ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አባላት የነበሩ ወታደሮች እና የመከላከያ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች “ደማችን ለጀግናችን” በሚል መሪ ቃል ደም ለግሰዋል፡፡

በሰሜን ዕዝ የሰራዊት አባላት ላይ በህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የተፈፀመው ክህደት ተግባር እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

አባላቱ “ጦርነትን የማይናፍቀው ግን ደግሞ ጦርነት ሲገጥመው እንደ አራስ ነብር አስፈሪነቱን በተግባር የሚያሳየው ሰራዊታችን ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ ባለበት ወቅት ደም በመለገሳችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡

በሠራዊቱ ላይ ጥቃት የፈፀመው የህወሃት ቡድን ተደምስሶ ለፍርድ እስኪቀርብ ድረስ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ እንቆማለን ሲሉም ተናግረዋል።

የእናት ጡት ነካሹ የህውሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን ላይ የፈፀመው ክህደት እና ጥቃት እጅግ አስቆጥቶናል በመሆኑም በማንኛውም መልኩ ከሠራዊታችን ጎን ቆመን መስዋዕትንት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።

እንዲሁም የመከላከያ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾችና አሰልጣኞችም ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ደም ለግሰዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አቶ ዮሀንስ ሳህሌ የህወሓት ሕንፈኛ ቡድን ሀገርን በሚያገለግለው ሰራዊት ላይ ጥቃትና ክህደት በመፈፀሙ ማዘናቸውን ተናግረዋል።

በሌላ ዜና አቶ ዳዊት ሀይለማሪያም የተባሉ ግለሰብ 18 ሺህ 800 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት መለገሳቸው ተገልጻል።

አቶ ዳዊት እንደተናገሩት መከላከያ ማለት ሀገር ማለት ስለሆነ በዚህ ወቅት ከጎንህ ነን ለማለት ነው ድጋፉን ያደረግነው ብለዋል።

ድጋፉን የተረከቡት ሜጀር ጄነራል ታደሰ መኩሪያ በበኩላቸው፥ ሠራዊቱ በህግ ማስከበር ግዳጅ ላይ እያለ ይህንን ድጋፍ በማበርከታቸው ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ስጦታውም ለብሔራዊ ድጋፍ አስባሳቢ ኮሚቴ ገቢ እንደሚደረግ መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.