Fana: At a Speed of Life!

ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች በአጭር ጊዜ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ – የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በፈጠረው ችግር ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ ሃገራቸው በመመለስ መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የተቋሙ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ደህንነትና ክብር ቅድሚያ በመስጠት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ የማስከበር እርምጃውን የጀመረው ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚያዋስኑ ከተሞች አካባቢ በመሆኑ ዜጎች ወደ ሱዳን መግባታቸው ነው የተገለጸው።

ኮሚሽኑ በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ ሃገራቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

ኮሚሽኑ የመከላከያ ሰራዊቱ ነጻ ያወጣቸው የትግራይ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብና በሰሜን ትግራይ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ የሚያደርግ ግብረ ኃይል ማሰማራቱንም ጠቅሰዋል።

ግብረ ኃይሉ የተፈናቃይ ዜጎችን ትክክለኛ ቁጥርና የሚያስፈልገውን ድጋፍ ትክክለኛ መረጃ ይሰበስባል ተብሏል።

ይሁንና ነጻ ያልወጡ አንዳንድ አካባቢዎች ለንጹሃን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር ምትኩ ገልጸዋል።

በሰሜኑ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅርቦት መኖሩንም አረጋግጠዋል።

በደቡብ ክልል ኮንሶና በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል አካባቢ ለተፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.