Fana: At a Speed of Life!

የህወሃት የጥፋት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን ክህደት የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አወገዙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሃት የጥፋት ቡድን በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ክህደት የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት አወገዙ።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የህወሃት የጥፋት ቡድን በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ድርጊት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ህወሃት በሰራዊቱ ላይ የፈፀመው ጥቃት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለውና ማንም ኢትዮጵያዊ የማይቀበለው እኩይ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በሰራዊቱ ላይ ልዩነቶችን ለመፍጠር የሚሰሩ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ወንጀለኞችም በህግ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሌተናል ጄነራል ሞላ ሃይለማሪያም በበኩላቸው÷ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን የፈፀመው ወንጀል ዘግናኝ እና ፍፁም አረመኔያዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጊቱ የህወሃት ጁንታ ሴራ እንጂ የትግራይን ህዝብ የማይወክል ስለመሆኑም ያብራሩ ሲሆን÷ወንጀለኛውን ቡድን ከማውገዝ ባለፈ በህግ ማስከበር ሂደት ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
ሰራዊቱን ያወያዩት ሌተናል ጄነራል ዮሃንስ ገብረመስቀል እንዳሉት ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን የአገር መከታ የሆነውን ሰራዊት በክህደት ጭፍጨፋ ፈፅሟል ብለዋል።
ድርጊቱ ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ የከህደት ወንጀል መሆኑን ገልፀው ህወሃት ወንጀሉን የፈፀመው ህዝቡ እርስ በርስ እንዲጫረስና ኢትዮጵያ እንዲትፈርስ አልሞ የነበረ ቢሆንም አልተሳካለትም ብለዋል።
ቡድኑ የኢትዮጵያዊያንን የአንድነት እና ሉዓላዊነት ሰነ ልቦና ባለማወቁ የወጠነው ሴራ ከሽፏል፤ መንግስት የተጀመረው የህግ ማስከበር ሂደትም ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡
የህግ ማስከበር ስራውን ጊዜ ሳይወስድ በፍጥነት ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.