Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ለአውሮፓ ሃገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል እየተወሰደ ስላለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ገለጻ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ ሃገራት አምባሳደሮች መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ስላለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ማብራሪያና ገለጻ አደረጉ።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ለህግ ማስከበር ዘመቻው መንስኤ፣ ዝርዝር ሁኔታው እና ስለዘመቻው ግብና አላማ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ዘመቻው በትግራይ ክልል ህግና ስርአትን የማስከበርና በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥቃት የፈጸሙ የህወሓት ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ አላማ እንዳለው አስረድተዋል።

አያይዘውም እየተካሄደ ያለው ዘመቻ የህወሓትን ጁንታ ከትግራይ ህዝብ በለየ መልኩ በንጹሃን ላይ ጉዳት ሳያደርስ ግቡን እንደሚያሳካም ተናግረዋል።

የህወሓትን ጁንታና የትግራይን ህዝብ በአንድ መመልከት ስህተት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ህወሓት የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ ማድረጉም ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

ገለጻውን የተከታተሉ የአውሮፓ ሃገራት አምባሳደሮች በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ህግና ስርአትን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚረዱ አንስተዋል።

በተጨማሪም መንግስት ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረትና በትግራይ ክልል እየወሰደ ያለውን ዘመቻ ጎረቤት ሃገራት እንዴት እንደሚመለከቱት ያላቸውን ስጋት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.