የሀገር ውስጥ ዜና

መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለመቀልበስ የሚነዛው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት የለውም- ብልፅግና ፓርቲ

By Meseret Awoke

November 21, 2020

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለመቀልበስ የሚነዛው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል አለ ብልፅግና ፓርቲ፡፡

ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዛሬም በድል ታጅቦ ህግ የማስከበር ስራውን ቀጥሏል፡፡

ይህን እርምጃ ወደ ኋላ ለመቀልበስ በየአቅጣጫው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ከመንዛት ጀምሮ አቅጣጫ የሚያሰቀይር እኩይ ተግባር መፈጸም የመንግስትን አቅም ያጠነክረው ይሆናል እንጂ ወደ ኋላ የሚመልሰው አይሆንም ብሏል ፓርቲው፡፡

መንግስት በትግራይ የመሸገውን የጥፋት ቡድን ለፈጸመው ክህደት የሚመጥን ህጋዊ እርምጃ እስኪወሰድበት ድረስ ወደ ፊት መገስገሱን ይቀጥላል ሲልም ነው ያስታወቀው፡፡

ኢትዮጵያ የግለሰቦች መፈንጫና የወንበዴዎች መደበቂያ አትሆንም፤ ይህንንም ንጹሃን ላይ ግፍ የፈጸሙትን ለህግ በማቅረብ ለህዝባችን በተግባር እናሳያለን ብሏል፡፡

በመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ መንግስት ድርድር ሊጀምር ነው በሚል የሃሰት ወሬ ማሰራጨት ግለሰቦች ምኞታቸውን የገለጹበት ካልሆነ በስተቀር መንግስት ከወንጀለኛ ጋር ድርድር እንደማይቀመጥ መገንዘብ ይገባል ነው ያለው፡፡

የአገራችን ህዝብም በየአቅጣጫው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለከፈለውና እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት አጋርነቱን እያሳየ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዛሬም እንደትናንቱ ለአንድነታችንና ለሰላማችን ሳንካ የሆነው እክል እስኪነቀል ድረስ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ይህን የጥፋት ቡድን ከህዝባችን ጫናቅ ላይ በማስወገድ አገራችንን ወደፊት ማሻገር ላይ መረባረብ ይገባቸዋል ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡