የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከየም ልዩ ወረዳ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በየም ልዩ ወረዳ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር በሳጃ ከተማ ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በውሃ፣ በመንገድ በትምህርት በጤና እንዲሁም በሌሎችም የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ዙሪያ መሻሻል ስላለባቸው ነጥቦች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አና የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በሰጡት ምላሽ፥ በልዩ ወረዳው በትምህርት ዘርፍ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ከዳር ለማድረስ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ክልሉ ያለውን ውስን ሀብት ታሳቢ በማድረግም ቅድሚያ የሚሹ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይሁን አሰፋ በበኩላቸው፥ የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት በመቻሉ ደስታቸውን ገልፀው፤ በልዩ ወረዳው የአፈር እና ውሀ ጥበቃ ስራ በመሰራቱ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።
ይህም የግልገል ጊቤ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
የልዩ ወረዳውን ህዝብ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የተቀናጀ የልማት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በየም ልዩ ወረዳ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችችንም ጎብኝተዋል።