Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ አመት የምስረታ በዓሉን አከበረ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ አመት የምስረታ በዓሉን አከበረ፡፡
ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ኩሪፍቱ ሪዞርት በተከበረው በዓል ላይ የተቋሙ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና አቶ ደግፌ ቡላ፣ የፋና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፣ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰጠኝ እንግዳው፣ የቀድሞው የቦርድ አባል አቶ ደሳለኝ መኮንን፣ ሰራተኞች፣ አጋር አካላት እና ተባባሪ አዘጋጆች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩም የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና የፋና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ተቋሙ አሁን ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ የተሻለ ስፍራ ላይ ለመድረስ በርትቶ መስራት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
ፋና አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረሱ የስራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞቹና ተባባሪ አዘጋጆች የላቀ ድርሻ እንደነበራቸው ተነስቷል፡፡
በዝግጅቱ ለመስራች ሰራተኞች፣ ለቀድሞ ቦርድ አባላትና አመራሮች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
ከዚህ ቀደም የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ሲያከብር መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ፋና ባለፉት 25 አመታት በተለይም በሬዲዮ ዘርፍ ኤፍ ኤሙን ጨምሮ በሃገር አቀፍ ስርጭቶቹ በዜና እና በተለያዩ ፕሮግራሞች አድማጭ ተከታዮቹ ጋር ሲደርስ ቆይቷል፡፡
በዚህም ወቅታዊ፣ አዝናኝ እና አስተማሪ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ወደ አድማጭ ተከታዮቹ ደርሷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በድረ ገጹ ሰፊ የዜና ሽፋን እና መረጃዎችን በማጋራት በርካታ ተከታዮችን ያፈራ ሲሆን፥ በቅርቡ በጀመረው የቴሌቪዥን ስርጭትም በተለያዩ ቋንቋዎች ወደ ተመልካቾቹ እየደረሰ ይገኛል፡፡
በሬዲዮ ስርጭት አንድ ብሄራዊ ጣቢያ እና ክልሎቹን ጨምሮ 12 ኤፍ ኤም ጣቢያችዎችን በመክፈት ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም በድረ ገጽ አማርኛን ጨምሮ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሌኛ እንዲሁም በእግሊዝኛ እና ዓረብኛ ቋንቋዎች ለተከታዮቹ መረጃዎችን እያደረሰም ይገኛል፡፡
በቴሌቪዥን ስርጭትም በሃገር ውስጥ ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና ትግርኛ እንዲሁም በውጭ ቋንቋዎች በዓረብኛ ስርጭት ለተመልካቾቹ ወቅታዊ መረጃዎችን እና ፕሮግራሞችን እያቀረበ ነው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.