Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ በስሙ ከመነገድ ውጭ ምንም ያልፈየደለትን የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያው አድርጓል – የብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የህወሓት አጥፊ ቡድን ለዓመታት የህዝብ ሃብት ሲመዘብር፣ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጽምና የራሱን ኪስ ሲያደልብ ኖሮ ዛሬ የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ በስሙ ከመነገድ ውጭ ምንም ያልፈየደለትን የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያው ማድረጉን የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡

የእኩይነቱ ጥግ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ጋር በፍቅር ኖሮ ሳለ እንደተወረረና በጠላት እንደተከበበ አድርጎ ፕሮፓጋንዳ በመስራት ለስደት እየዳረገውና ድርብ በደል እያደረሰበት ይገኛልም ብሏል፡፡

መንግስት ይህ የወንበዴ ቡድን ለዓመታት ምሽግ ውስጥ አገርና ህዝብ ለመጠበቅ የኖረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው የውንብድና ተግባር መቼም ይቅር የማይባል እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡

ይህ ዓለም የሚያውቀው እውነታ ሆኖ ሳለ በማንአለብኝነት የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት ለመሸሸግ ትግራይ ተወራለች፣ ንጹሃን እየተገደሉ ነው በሚል ፕሮፓጋንዳ ስቦ ወደጦርነት ያስገባውን መንግስት ሲከስ እንደማየት አሳፋሪ ነገር የለም ነው ያለው ፓርቲው፡፡

ይህ እኩይነቱ ሳያንሰው መንግስት ህግና ስርዓት ማስጠበቅ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ በተጠና የወታደራዊ ስልት የማህበራዊ ተቋማትና የእምነት ተቋማትን ከጥቃት በጠበቀ ሁኔታ ይህ እኩይ ቡድን ለጥፋት ያዘጋጃቸው ቦታዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡

ሆኖም ይህ ቡድን የማህበራዊ ተቋማትና የእምነት ተቋማትን የመሳሪያ መሸሸጊያ በማድረግ መንግስትና ህዝብን ስህተት ውስጥ በመክተት ለመወንጀል ሲዳክር ይውላል ብሏል ፓርቲው፡፡

መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ የሚከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እንጂ ወደኋላ የሚመለስ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

ፓርቲው መንግስት ስለአገር መስዋዕት በሆኑ ንጹሃን ደም የሚደራደር ደካማ አድርጎ ማሰብና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ መንግስትን ለማዳካም ጥረት ማድረግ የጁንታው መጨረሻው የጣር ጩኸት ከመሆን የዘለለ ትርጉም የሌለው መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አንስቷል፡፡

ንጹሃን በጠራራ ጸሃይ ለማረድ፣ ለማሳረድ፣ አገር ለማፍረስ ያልራራ ይህ አጥፊ ቡድን ዛሬ በበወሬ ወለደ ታሪክ መንግስትን ለመወንጀል የቱንም ያህል ርቀት ቢጓዝ ባህሪውን በግልጽ ለመገንዘብ የበለጠ እድል የሚሰጥ እንጂ በመንግስት ዓላማ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር እንደማይሆንም ገልጻል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝቡ መገንዘብ የሚገባው ይህ ቡድን ዛሬም ለቁማሩ ማስያዣነት እየተጠቀመ ያለው ንጹሃኑን የትግራይን ህዝብ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ህወኃት የእምነት ተቋማትን የመሳሪያ መሸሸጊያ ከማድረግ ጀምሮ የማህበራዊ ተቋማትን ጭምር ለእኩይ አላማው ማስፈጸሚያ የሚሆነውን የጦር መሳሪያ ማከማቻ አድርጓል ነው የተባለው፡፡

ይህ በሴራና በጥፋት የተካነ አጥፊ ቡድን ዓላማው ግልጽ ነው፡፡

አገር የመበታተንና ትግራይን አኬልዳማ የማድረግ ነው ብሏል የብልጽግና ፓርቲ፡፡

በመሆኑም መላው ህዝብ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ በውስጡ የተሸሸጉ ወንበዴዎችን ሴራ መገንዘብ ያስፈልጋል ሲል ነው የገለጸው፡፡

የህወሓት ጁንታ ቡድን ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ የሚወርድበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ ይገኛል፡፡

ጉዳዩ ህግ የማስከበርና አገር የማፍረስ ተልዕኮ ያለውን ይህ ጁንታ ለህግ ማቅረብ በመሆኑ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ንጹሃንን በመጠምዘዝ የትግራይ ህዝብ በአደባባይ ወጥተህ ተዋጋልኝ የሚል ጥሪ ማስተላለፉ ትግራይን አኬልዳማ የማድረግ ሴራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በመሆኑም መንግስት በብልሃትና ጥበብ በተሞላበት ወታደራዊ ስልት ይህን ጁንታ ከተደበቀበት ፈንቅሎ በማውጣት ለፍርድ እንደሚያቀረበው በመተማመን ሁሉም ለዚህ ዓላማ መሳካት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡

ይህ ቡድን የኢትዮጵያዊ ስነልቦና የሌለው ከራሱ ፍላጎት ውጭ ማሰብ የማይችልና በታግዬልሃለሁ ሰበብ ህዝብን ባሪያ አድርጎ መኖር የሚሻ የወንበዴ ቡድን መሆኑን ከድርጊቱና ከመጣበት የጥፋት መንገድ መገንዘብ ይቻላል፡፡

አሁን የመጨረሻው እስትንፋሱ ላይ በመድረሱ ድርጊቱ ሁሉ በንጹሃን ደም መቆመር በመሆኑ መንቃት እንደሚገባና ስለነጻነት የማያወቀው ነፃነት አዋጁ የህወሓት ጁንታ ቡድን በኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ ድባቅ ይመታል ብሏል ፓርቲው፡፡

ይህ በቅርቡ የሚፈጸም እውነት መሆኑን በግልጽ ማወቅ እንደሚገባም ብልጽግና ፓርቲ አስታውቋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.