Fana: At a Speed of Life!

በዛታ ግንባር ለጥምር ጦሩ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን ሥር የሚገኙ አስር ወረዳዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በደቡባዊ ትግራይ ዞን ዛታ ግንባር ተገኝተው ቁሳቁሱን ያስረከቡት የዞኑ አስተዳደር ተወካዮች ሕዝቡ እስከመጨረሻው ድረስ ከጥምር ጦሩ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን የገንዘብና ኢኮኖሚ መምሪያ ኃላፊ አቶ አስማረ ጀንበር እና የፋርጣ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ውለታው ጌራወርቅ ለጥምር ጦሩ ባስተላለፉት መልዕክት የዞኑ አስተዳደር እየተመዘገበ ባለው የድል ውጤት መደሰቱን ገልፀዋል፡፡

ደጀን የሚሆን ሕዝብ ከጎናቸው እንዳለም ነው ለጥምር ጦሩ ያረጋገጡት፡፡

ድጋፉን የተቀበሉት የሀገር መከላከያ፤ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት ግዳጃችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ወደመደበኛ የልማት ሥራ የምንመለስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል፡፡

ያለንበት ወቅት ሕግን ለማስከበር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን ያሉት አባላቱ የተደረገው ድጋፍ ለሠራዊቱ ጉልበትና አቅም እንደሚሆነው መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.