Fana: At a Speed of Life!

የትራምፕ አጋሮች ፕሬዚዳንቱ በምርጫ መሸነፋቸውን አምነው እንዲቀበሉ እየጠየቁ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የፕሬዚዳንት ዶናልድ የትራምፕ የቅርብ አጋሮች ፕሬዚዳንቱ በምርጫ መሸነፋቸውን አምነው እንዲቀበሉ እየተማጸኗቸው ይገኛሉ፡፡

ሽንፈታቸውን እንዲያምኑ ከወተወቷቸው ሰዎች መካከል የቀድሞ የኒው ጀርሲ ገዢ ክሪስ ክሪስቲ ዋነኛው ናቸው ተብሏል፡፡

ክሪስ ክሪስቲ የህግ ጉዳዩን የያዘውን የትራምፕ ቡድን ድርጊት “ብሔራዊ ውርደት” ነው በማለት ነበር የገለጹት፡፡

እንዲሁም የትራምፕ ቡድን ከፍርድ ቤት ውጪ ስለምርጫው መጭበርበር ቢያወራም ችሎት ላይ ሲቆሙ ግን ጭብጥ አንስተው ሲሟገቱ አይታም ነው ያሉት፡፡

በተካሄዱት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ድምጽ እንደሰጡ የተናገሩት ክሪስ ክሪስቲ ምርጫ ውጤት አለው፤ ውጤቱንም መቀበል ግዴታ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ክሪስ ክሪስቲ በተጨማሪም የባይደንና የትራምፕ የመጀመሪያ ክርክር ወቅት ፕሬዚዳንት ትራምፕን ከረዷቸው ሰዎች መካከል አንዱ ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የትራምፕ የምርጫ ቡድን በፔንሲልቫንያ ይግባኝ ጠይቋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ትራምፕ በግዛቲቱ በፖስታ የተሰጡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ድምጾች ውድቅ እንዲደረግላቸው ክስ አቅርበው ነበር፡፡

ሆኖም ጉዳዩን የተመለከቱት ማቲው ብራን የተባሉት ዳኛ በትራምፕ የቀረበው ክስ ጭብጥ የሌለው ነው በማለት ውድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

እስካሁን በሁሉም ግዛቶች በተካሄደው የድምጽ ቆጠራ ባይደን በ5 ነጥብ 9 ሚሊየን ብልጫ አላቸው ተብሏል፡፡

እንዲሁም የግዛቶቹን ውክልና በሚይዘውና ወሳኝ በሆነው ድምጽ ደግሞ ባይደን 306 ድምጽ ሲይዙ ትራምፕ 232 ድምጽ ነው ያገኙት፡፡

 

 

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.