ቋሚ ኮሚቴው መንገዶች በጥራት እንዲገነቡ አሳሰበ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ-አደር እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በአርብቶ-አደር እና ከፊል አርሶ-አደር አካባቢዎች የሚገነቡ መንገዶች በጥራት እንዲገነቡ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ፕሮጀክቶች የ2013 በጀት ዓመት የአንደኛውን ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ የገመገመ ሲሆን÷ የመንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ጥራት ትኩረት የሚገባው ዋና ጉዳይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ እንዳሉት በሪፖርቱ ከእነአፈጻጸም ልዩነታቸውም ቢሆን የእያንዳንዱ ፕሮጄክት የበጀት አጠቃቀም እና የዕቅድ አፈጻጸም ግልፅ ሆኖ መቅረቡ፣ በመንገድ ፕሮጀክቶች አማካይነት የተፈጠረው የሥራ ዕድል በዝርዝር መቅረቡ መቀጠል አለበት፡፡
ሰብሳቢዋ አክለውም የአፈጻጸም ውስንነት ያለባቸውን ፕሮጄክቶች በመለየት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ የአርብቶ አደር እና ከፊል አርሶ አደር አካባቢዎች በዕቅድ በመሥራት ጥራትን እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን በትኩረት መከወን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የወሰን ማስከበር ችግርን ለመፍታት በሚደረጉ ርብርቦችም፤ ምክር ቤቱ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የፀጥታ እና ወሰን የማስከበር ችግር፣ የውጭ ምንዛሪ እና የሲሚንቶ ዕጥረት ለመንገድ ፕሮጄክቶቹ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ፕሮጄክቶች ጨረታ ከሚሳተፉ ተቋራጮች መካከል ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረቡት ተጫራቾች እንዲያልፉ ስለሚደረግ ለመንገድ ፕሮጄክቶች መጓተት እና ጥራት መጓደል ምክንያት ናቸው ማለታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡