Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት በምታደርገው ጥረት ቻይና ከጎኗ ቆማለች – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት እና ብልጽግናን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት ቻይና ሁልጊዜም ከጎኗ እንደምትቆም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ እና ቻይና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምሥረታ 50ኛ ዓመት አስመልክቶ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደ ውይይት ላይ ነው፡፡

ውይይቱ ያተኮረው ሁለቱ ሀገራት ባላቸው ታሪካዊ ጉዳዮችና አሁን ባለው የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው ላይ ነው ተብሏል፡፡

ውይይቱ “ለአፍሪካ ቻይና ግንኙነት ኢትዮ-ቻይና ሁሉን ዓቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር ሞዴል በሚል እና የደቡብ ደቡብ ትብብር” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው፡፡

እንዲሁም ሃገራቱ ከዚህ በፊት ባልተሰማሩባቸው ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ያለመ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም የቻይና ኢንቨስትመንት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በቱሪስት መስህብ ፓርኮች፣ በሳተላይት ቴክኖሎጂ የሚያደርጉት ትብብር የግንኙነታቸው ዕድገት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ የንግድ እና የኢኮኖሚ ትብብር መመስረታቸውን አንስተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያመዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ሊያገኙ የሚችሉትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አብራርተዋል፡፡

የቻይና አፍሪካ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የሁጅያን ግሩፕ ፕሬዚዳንት ቻይናውያን በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በተሰማሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደርና አቶ ተሾመ ቶጋ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዚሃይዩዋን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጋራ መከባበርና በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.