Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በማንኛውም ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትሆን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሩሲያ የወዳጅነት ቡድን ጋር በዛሬው ዕለት ባካሄዱት ውይይት፤ ሩሲያ በማንኛውም ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትሆን ገለጸች፡፡

ሩሲያ ይህንን የገለጸችው አራት አባላትን የያዘውን የልዑካን ቡድን መርተው ከቋሚ ኮሚቴው ጋር በተወያዩት አምባሳደር ኤቭጊኒ ቴሬክሂን አማካይነት ነው፡፡

አምባሳደሩ አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሀገራዊ ሁኔታ ሩሲያ እንደምትገነዘብ አስታውሰው፤ በየትኛውም ሁኔታ ከጎንዋ በመሆን ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

አምባሳደር ቴሬክሂን አክለውም፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመረዳዳት እና በመተማመን የተመሠረተ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት የቆየ መሆኑን በድጋሚ አስታውሰው፣ ይህ የቆየው ወዳጅነት እንዲጠናከር በጋራ ልንሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ጦርነት እያካሄደች ሳይሆን የሕግ የበላይነትን የማስከበር እና ሰላምን የማረጋገጥ ዘመቻ ላይ መሆኗን ገልጸው፤ ሰላምን በማስከበር የሚታወቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የጀመረውን የሰላም ማስከበር ሥራ በአፋጣኝ እያጠናቀቀ በመሆኑ ሀገሪትዋ ወደነበረችበት ሰላም እንደምትመለስ አስገንዘበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በዚህ ሩሲያ ምንም ስጋት ሊገባት አይገባም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩልም ይህንን ግንኙነት በሁሉም መስክ ማለትም፤ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር አጠናክሮ ማስቀጠል የወዳጅነት ኮሚቴው የትኩረት ማዕከል ሊሆን እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ከተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.