Fana: At a Speed of Life!

የጀርመን መንግስት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ትክክለኛ ገጽታ እንዲረዳ ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የጀርመን መንግስት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ትክክለኛ ገጽታ እንዲረዳ መደረጉን በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ገለጹ።
አምባሳደሯ በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ለጀርመን መንግስት ባለስልጣናት፣ ለፓርላማ አባላትና ለዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ማብራሪያ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የሕግ ማስከበር እርምጃውን አስመልክቶ የሚያወጣቸውን ወቅታዊ መረጃዎች ለጀርመን መንግስት የማሳወቅ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተሰጡ ማብራሪያዎች የጀርመን መንግስት በትግራይ እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ትክክለኛ ገጽታና መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መረዳቱንም ነው አምባሳደር ሙሉ የገለጹት።
የሰብአዊ ቀውስ ሊኖር ይችላል በሚል ለተነሳው ሀሳብም መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ እንደሚገኝና ሰብአዊ ድጋፍ ሊደርጋቸው የሚችልባቸው ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን መገለጹን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሠላም የኖቤል ሽልማትና አሁን በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃን አስመልክቶ በጀርመን መንግስት በኩል ሀሳቦች መነሳታቸውን አመልክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠላም የኖቤል ሽልማት ሀሳብ ለሠላም ባበረከቱት አስተዋጽኦ ያገኙት እንደሆነና አሁን በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለው እርምጃ አገርን ለመጠበቅና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚደረግ በመሆኑ ምንም አይነት የሚጋጭ ነገር እንደሌለው በመግለጽ ሁኔታውን እንዲረዱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የጀርመን መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ገለጻ የተደረገላቸው አካላት ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዲደናቀፍ እንደማይፈልጉና ለለውጡ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
የተወሰኑ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን ለአንድ ወገን ያደላ ዘገባ እያቀረቡ እንደሚገኙና ይህንንም ጉዳዩ ለሚመለከተው የጀርመን መንግስት አካል በማሳወቅ እንዲያስተካክሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በጀርመን የሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.