Fana: At a Speed of Life!

ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ የነበረ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ የነበረው ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ተጠርጣሪው ተፈራ በላይ ወይም እንድሪስ በመባል የሚታወቅ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስመዝግቧል።

የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው በርካታ መጠሪያ ስም እንዳለው ገልጿል።

ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረበው ተጠርጣሪም በኦሮሚያና በአማራ ክልል የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ሲዘጋጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌደራል ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

ፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪው በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ኡርጌሳ አካባቢ ህዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም መያዙን ነው የገለጸው፡፡

ፖሊስ ተጠርጣሪው ከአይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው እና ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ የሽብር ድርጊት የሚፈጽሙ አባላትን ሲመለምል እንደነበርም ጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በዚሁ ተግባር ተጠርጥረው ለታሰሩ እስረኞች ብር ሲያከፋፍል እንደነበርም ነው ፖሊስ ለችሎቱ ያስረዳው።

ተጠርጣሪው በበኩሉ በድርጊቱ ተሳትፎ እንደሌለው ለችሎቱ ያስረዳ ቢሆንም ፖሊስ በወንጀሉ መሳተፉን የሚያስረዳ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን ተናግራል።

ፖሊስ ለችሎቱ የቀሪ ምስክር ቃል እና ተባባሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ፍርድቤቱም ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

በሌላ በኩል ከሮቤራ ሆቴል ሽያጭ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በዚሁ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ተከሳሹ ከዚህ በፊት ዐቃቤ ህግ ባሰማባቸው ምስክር ላይ ዝርዝር የመከላከያ ማስረጃ ለማቅረብ ለታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.