Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ የጀግኖችና የሕፃናት አምባ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቋቋመ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ትብብር “ብሔራዊ የጀግኖችና የሕፃናት አምባ” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት መቋቋሙ ተገለፀ።

ድርጅቱ የተቋቋመው በጦር ሜዳ ጉዳት ለደረሰባቸው አባላት እንክብካቤ ለማድረግና የሕይወት መሥዋዕትነት የከፈሉ የሠራዊት አባላት ልጆችን ሰብስቦ ለማሳደግ ነው ተብሏል።

ይህም ቀድሞ በጀግኖች አምባ የነበሩትን የጦር ጉዳተኞችን የሚያጠቃልል መሆኑ ተጠቁሟል።

ድርጅቱ በቦርድ የሚተዳደር ሲሆን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተሰኘው ድርጅት፥ ለድርጅቱ መቋቋም ከፍ ያለ ሚና እንደነበረው የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።

አዲሱ ብሔራዊ የጀግኖችና የሕፃናት አምባ በዘለቄታነት ዘመን ተሻጋሪ ድርጅት እንዲሆን ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ የሀገር ባለውለታ የሆኑ የጀግኖች አምባ በመፍረሱ፣ ለሀገራቸው ሲሉ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን አስታውሰዋል።

አምባውን በአዲስ መልኩ በማቋቋም የራሱ የሆነ የገቢ ምንጮች እንዲኖሩትና ጀግኖችና የሰማዕታት ልጆችን በቋሚነት ማገዝ የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች ታሪካዊ ሀላፊነት በመሆኑ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የጦር ሀይሎች ሆስፒታል አዛዣ ብርጋዴር ጄኔራል ሀይሉ እንዳሻው በቅርቡ በአዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ መንግስትም የጀግኖችና የህፃናት አምባን ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተለይም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ከተቋሙ ጋር በመሆን ድርጅቱን በመመስረታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ለሀገር ክብርና ለሉዓላዊነት በጦር ሜዳ ጉዳት ለሚደርስባቸው ወታደሮችንና ቤተሰቦች በዘላቂነት ለማገዝ የሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስም ለዓላማው መሳካት መከላከያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.