Fana: At a Speed of Life!

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተላከው በመግለጫ÷ ርዕሰ መስተዳድሩ ህገ ወጡ የወያኔ ጁንታ ቡድን በኢትዮጵያ ብሄር ብሄርሰቦችና ህዝቦች ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም እንደነበር ሀገር ያወቀው ጸሃይ የሞቀው ሀቅ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ለመስማት እንኳን የሚዘገንኑ ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችን፣የተደራጀ የሀገር ሀብት ዝርፊያ፣የዜጎች መፈናቀል፣አካል ማጉደል፣አሰቃቂ ግድያዎችን መፈጸም፣ባጠቃላይ አሰቃቂ ኢ-ሰብዓዊ የመብት ረገጣ መፈጸም የዚህ ሰው በላና ህገ ወጥ ጁንታ የሰርክ ተግባር እንደነበር ህዝባችን ከማንም በላይ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሀቅ ነው ብለዋል።
ዘራፊው፣ከሃዳዊው የወያኔ ጁንታ ህዝቦች ላይ ሲፈጽመው የነበርው የበደል ጽዋ ሞልቶ በመፍሰሱ ህዝቡ በምሬት ከቤቱ ፣ከጫፍ እስከጫፍ ነቅሎ በመውጣት ይሄን ሰው በላ፣ከሃዲና ዘራፊ ቡድን አንቅሮ በመትፋት ሲታገልው እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነውም ነው ያሉት።
በህዝቡ ግፊትና በለውጡ አመራር ሳቢነት በኢትዮጵያ በተቀጣጠለውና በተፋፋመው የለውጥ እንቅስቃሴ የጁንታውን መረብ/ኔትወርክ በመበጣጠስ ህዝቡ የባርነት ቀንበሩን ከላዩ ላይ አሽንቀንጥሮ በመጣል ይህን ዘራፊ፣ገዳይና ከሃዲ ጁንታ ለአንዴና ለመጨረሻ ከላዩ በማስወገድ ጥግ እንዲይዝ አድርጓልም ነው ያሉት።
ሆኖም ጁንታው ባለፉት ጊዜያት ሲፈጽማቸው የነበራቸውን በደሎች ለሀገር አንድነትና ሰላም፣ለወንድማማችነት መቻቻል፣ሲባል፡የለውጡ አመራር በሆደ ሰፊነት እና በትዕግስት በማየት/በማለፍ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙትን እኩይ የቡዱኑ አስከፊና አሰቃቂ በደሎችን ሁሉ በመደመር ዕሳቤና በፍቅር እንዲታከሙ በሰፊው ጥረት ቢደረግም ይህን የመንግስትን ታጋሽነት ይህ ከሃዲ ቡድን እንደ ፍርሃት በመቁጠር የሀገር አንድነት ዓርማና የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መመኪያና ጋሻ የሆነውን ጀግናው የመከለካያ ሰራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ የፈሪ ዱላ በማሳረፍ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመፈጸም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ከጀርባ ወግቷል ሲሉ ገልጸዋል።
ይሄም በሀገራችን ጥቁር ጠባሳ የሆነ ትልቅ የክህደት ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
ይህ ከሃዲ፣ዘራፊ ጁንታ ቡድን መላው ሀገሪቱ ወደ ትርምስ ለማስገባት እንድ ኦነግ ሸኔ አይነት ተላላኪና ቅጥረኛ የጥፋት ሀይሎችን መልምሎ በማሰለፍ የፋይናንስና የሎጄስቲክ ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያን በመውጋት ጸረ-ኢትዮጵያዊነቱን በተግባር ያረጋገጠ ኢትዮጵያዊያንን በመግደል፣በመዝረፍ ሀገርን የሚያተራምስና የሚበጠበጥ የእኩይ ሴራ ባለቤት ቡድንም ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ሀገራችን ላይ በተፈጸመው ክህደት ህግን የማስከበር ግዳጅ/ዘመቻ ላይ የሚገኘው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት በሁለት ምዕራፎች ላስመዘገባቸው አንጸባራቂ ድሎች እና ለከፈለው እየከፈለ ላለው አኩሪ መስዕዋትነት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ታላቅ ምስጋና እና አክብሮት ያለው መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁም ብለዋል አቶ ሽመልስ።
አያይዘውም ህዝቡም በመከላከያው ላይ የተፈጸመው የክህደት ክህደት ድርጊት አስቆጥቶትና አስቆጭቶት በራሱ ተነሳሽነት ታላላቅ የከሃዲው ጁንታ የክህደት ድርጊት ውግዘትና የመከላካያ የድጋፍ ሰልፎችን በማድረግ፡ደም በመለገስ፣በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የእርድ ሰንጋዎችና ፍየሎችን በማቅረብ፣እንዲሁም የገንዘብ መዋጮ በማድረግና እስከ ህይወት መስዕዋትነትም ከጎኑ በማሰለፍም ለጀግኖች ልጆች ያሳየው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነውም ነው ያሉት።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ከሃዲውና ዘራፊው ጁንታ ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ህዝቡን የሚወጉ የወያኔ ትሮይ ተላላኪና ቅጥረኛ የኦነግ ሸኔ ላይ በኦሮሚያ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ፖሊስ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ አንጸበራቂ ድሎችን በማስመዘገብ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ህግን የማስከበር ተልዕኮውን በድል አጠናቆ ወደ ቀድሞው መደበኛው ስራው እስኪመለስ ድረስ ህዝቡ እስከ ህይወት መስዕዋትነት ከጀግናው መከላከያ ጎን ለመቆም የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል፣ኦነግ ሸኔን በመጠራረግ ህዝቦች፣በወንድማማችነት፣በዕኩልነት፣በፍቅርና በሰላም የሚኖሩባት ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ለማስቀጠል እንዲሁም እውን ለማድረግ የጀመርነው የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጥላችኋለው ብለዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.