Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ገቢን በማሻሻል ህብረተሰቡን እኩል ተጠቃሚ ያደርጋል- ወይዘሮ አዳነች    

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በገቢዎች ሚኒስቴርና በገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሸያ አዋጅ ላይ ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማሰባሰብና ግልፅነት ለመፍጠር የሚያስችል የፓናል ዉይይት እየተካሄደ  ይገኛል፡፡

የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የገቢዎች  ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዉይይቱ ግልፅነት የሚያስፈልጋቸዉ ጉዳዮችን ለማብራራትና ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማካተት ታልሞ  የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የገቢ አሰባሰቡን ለማሻሻልና ለማዘመን መንግስት መጠነ ሰፊ ማሻሸያዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የገቢ አሰባሰቡ እየተሻሻለ መምጣቱ፣ ህጋዊነትን በማበረታታት የንግዱ ማህበረሰብ የህግ ተገዥነት መሻሻሉ እና ግዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት አሰጣጦች ተስፋ ሰጪ እየሆኑ መምጣታቸዉን  ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ ማሻሸያ ረቂቅ አዋጅ ገቢን በማሻሻል ህብረተሰቡ ላይ የታለመለትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለዉጦችን በማምጣት ህብረተሰቡን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ የታክስ መሰረትን በማስፋትና ተደራራቢ ታክስን በማስቀረት የዉጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት ፡፡

በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች  ኢትዮጵያ ከሃገራዊ ምርት 0 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ በመሰብሰብ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኑን ተገልጿል፡፡

የረቂቅ አዋጁ ሰነድ በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ሙላት ወልዱ ቀርቦ ዉይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡

በፓናል ዉይይቱ ላይ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ የሚገኙ  ሲሆን የረቂቅ አዋጁ ሰነድ  ቀርቦ ዉይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.