Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት ጁንታ ታጣቂ ሃይል በማይካድራ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቐለ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ ነው- ሜ/ጀኔራል መሀመድ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት ጁንታ ታጣቂ ሃይል በማይካድራ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቐለ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ተናገሩ።

የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ሁሉ ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ ድርጊቱን የሚፈጽመው ልዩ ቡድን አዘጋጅቶና በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ያዘጋጀውን የመከላከያንና የኤርትራ ሰራዊት ዩኒፎርሞችን በማልበስ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

ሜጀር ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ይህን ያሉት ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ነው።

የህወሓት ፅንፈኛ ሃይል በየጊዜው እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝብን እያደናገረ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

ለአብነትም ቡድኑ ከቀናት በፊት “በራያ ግንባር 21ኛ ክፍለጦርን ደምስሰናል፤ አድዋ ላይ የመጣውን ሃይል በመደምሰስ አካባቢውን ተቆጣጥረናል” ሲል መናገሩን አንስተዋል።

ነገር ግን በእለቱ እርሳቸውን ጨምሮ የሰራዊቱ አመራሮች በተገለጹት ስፍራዎች ላይ በመገኘት ለመገናኛ ብዙሃን ገለጻ ማድረጋቸውንና ገለጻውም አየር ላይ መዋሉን ነው የተናገሩት።

ይህም የጁንታውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የቡድኑ አፈቀላጤዎች ተደብቀው መግለጫ ከመስጠት ይልቅ እውነታቸውን ከሆነ “ደምስሰን አስለቅቀናል” ባሏቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት መግለጫ መስጠት በቻሉ ነበር ብለዋል።

የቡድኑ መሪዎች ህግ የማስከበሩን ዘመቻ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ህዝባዊ ጦርነት ለማስመሰል እየጣሩ መሆኑንም አውስተዋል።

ነገር ግን የትግራይ ህዝብ ዘመቻው ጽንፈኛ ቡድኑን ብቻ እንደሚመለከት በተግባር ማሳየቱን አብራርተዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተግባር ከማሳየቱም በላይ ጁንታው ምን ያህል ሲበድላቸው እንደቆየ እየገለጸ ይገኛልም ነው ያሉት።

የህወሓት የጥፋት ሃይል ያሰበው ሴራ ሁሉ እየከሸፈበት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ደግሞ አዲስ የጥፋት እቅድ ማውጣቱን ደርሰንበታል ብለዋል ሜጀር ጀኔራል መሀመድ።

በዚህም በማይካድራ ንፁሃን ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቐለ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ድርጊቱን ለመፈጸም ደግሞ ልዩ የገዳይ ቡድን ማዋቀሩንም ነው የተናገሩት።

የገዳይ ቡድን አባላቶችን በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አማካኝነት ያዘጋጀውን የኢፌዴሪ መከላከያ እና የኤርትራ ሰራዊት ዩኒፎርሞችን በማልበስ ጭፍጨፋውን ለመፈጸም መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

ቡድኑ ይህን የሚያደርገው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰራዊት በጋራ በመሆን ንፁሃንን እንደጨፈጨፉ በማስመሰል ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት መሆኑንም ነው ያነሱት።

ይህም የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ከስልጣን ውጭ ለህዝብ ምንም አይነት ርህራሄ እንደሌለው አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል።

ቡድኑ በየጊዜው የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ተስፋ መቁረጡን የሚያመላክቱ ስለመሆናቸውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ ክደው ከጽንፈኛ ቡድኑ ጋር የተሰለፉ የሰራዊቱ አባሎችም ሆኑ ቡድኑ ያደራጃቸው ታጣቂዎች በሁሉም ግንባሮች በመሸነፍ ወደ መቐለ እንደሸሹም ነው የተናገሩት።

በትግራይ ክልል ሰራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች እንዳደረጉት ሁሉ የመቐለ ነዋሪዎችም ውግንናቸው ለሰራዊቱና ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ተገደው ለቡድኑ እየተዋጉ ያሉ ታጣቂዎችም በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለሉ በአቅራቢያቸው ላለው የመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሰራዊቱ እያከናወነው ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ረገድ እያደረገው ላለው አስተዋጽኦም ሜጀር ጀኔራል መሀመድ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.