Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የህወሓት ቡድን በማይካድራ የፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት ተግባር አወገዘ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ መንግስት ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት ተግባር አወገዘ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ሪፖርት፥ የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ሀይሎች በማይካድራ በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙት ጭካኔ የተሞላበት ተግባር እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ልብ ሰባሪ መሆናቸውን መንግስት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ሪፖርት ከዚህ ቀደም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት የሚያረጋግጥ መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ያመላክታል።

ተግባሩ ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ እየፈፀመ ያለው ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ምን ያክል እንደሆነም የዓለም ህዝብ በድጋሚ ያረጋገጠበት ነውም ብሏል ባወጣው መግለጫ።

የኮሚሽኑ ሪፖርት የማይካድራው ጥቃት ተራ የወንጀል ተግባር ሳይሆን በእቅድ እና በተቀናጀ መንገድ የተፈፀመ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተግባር መሆኑንም ጠቅሷል።

የህወሓት ሀይሎች ሳምሪ ከተባለ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበር ዝግጅት በማድረግ እና በማቀድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አረጋግጧልም ብሏል መንግስት።

እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት የህወሓት ህገ ወጥ ቡድን የፈፀመው ተግባር በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል ብሏል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን ጭካኔ የተሞላበትን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲያወግዝም መንግስት ጥሪ አቅርቧል።
የዚህን ወንጀል ፈፃሚዎችም ለህግ የሚያቀርብ መሆኑንም መንግስት በመግለጫው አረጋግጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.