Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት የጥፋት ቡድን በማይካድራ የፈፀመውን አይነት እኩይ ተግባር በመቐለ ለመድገም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ኮሚሽኑ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት የጥፋት ቡድን በማይካድራ የፈፀመውን አይነት እኩይ ተግባር በመቐለ ለመድገም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡

ኮሚሽኑ የቡድኑ እኩይ ዕቅድ መረጃ እንደደረሰውም አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል የተጀመረው ሕግን የማስከበር እርምጃ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጠናቆ የመጨረሻውና ሦስተኛው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፅንፈኛው የህወሓት ጁንታ ቡድን መቐለ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ያልሆኑ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ለመፈፀም፣ ንብረታቸውን በመዝረፍ ለማቃጠል፣ የመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ በመልበስ ሰዎች ላይ በድንገት ተኩስ በመክፈት አስነዋሪ ድርጊት ለመፈፀም ማቀዱን ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

ቡድኑ ሰሞኑን በማይካድራ የፈፀመውን አስነዋሪና አሰቃቂ ጭፍጨፋ ለመድገም እቅድ አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና ይህንን እኩይ ተግባር ከፈፀመ በኋላም ድርጊቱ የተፈፀመው በመንግስት ነው ብሎ በሚዲያ ለማሰራጨት የተዘጋጀ መሆኑን ከህዝብ መረጃ ደርሶኛል ነው ያለው ኮሚሽኑ።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ይህንን የጥፋት ሴራ ተከትሎ ጁንታው ቡድን ሊያሰራጭ የተዘጋጀውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳና ይህንን እኩይ ተግባር አስቀድሞ እንዲረዳና ተቀባይነት ያጣ ዘንድ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ማሳሰብ እንወዳለን ሲል አስታውቋል።

ህዝቡ ማንኛውንም የተለየ እና አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ሲያይ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.