Fana: At a Speed of Life!

የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አተረፉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች በ2013 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አተረፉ፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር በፋይናንስ ዘርፍ የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ናቸው ትርፉን ያስገኙት።

የድርጅቶቹ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ አፈጻጸም ህዳር 8፣ 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም መገምገኙን ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ድርጅቶቹ የባንክና የመድን አገልግሎቶችን በመስጠት በሩብ ዓመቱ 19 ነጥብ 99 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው 18 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር ወይም የዕቅዳቸውን 95 በመቶ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

ከተገኘው አጠቃላይ ትርፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወይም ከዕቅዱ 78 በመቶ በማትረፍ 81 ነጥብ 23 በመቶ ያህል ድርሻ መያዙም ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ብር 455 ሚሊየን ወይም የዕቅዱን 23 ነጥብ 51 በመቶ ሲያተርፍ፣ ለዘርፉ አጠቃላይ ትርፍ የ11 ነጥብ 93 በመቶ አስተዋጽኦ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ 260 ነጥብ 56 ሚሊየን ወይም የዕቅዱን 75 በመቶ አትርፎ ለዘርፉ ትርፍ አፈጻጸም የ6 ነጥብ 83 በመቶ ድርሻ ማበርከቱ ተጠቅሷል፡፡

በየግምገማዎቹ ማጠቃለያ ላይ የድርጅቶቹ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት አፈጻጸም አበረታች በመሆኑ በቀጣዮቹ የ2013 በጀት ዓመት የትግበራ ምዕራፎች የየድርጅቶቹ ቦርዶች፣ የማኔጅመንት አባላትና መላው ሠራተኛ ይህንኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉና በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አቅጣጫ ተሰጥቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.